Monday, December 29, 2014

ዓመቱ በጥቂት ቃላት

ዓመቱ በጥቂት ቃላት
ይህ ዓመት በርግጥም ስኬታማ ነበር። ዓመታት የሚፈጁ ክንውኖችን በአስራሁለቱ ወራት ውስጥ እንዳካሂድ እግዚአብሔር በምትታይ እጅ ረድቶኛል።
ከነሐሴ አስራአምስት ጀምሮ ለሦስት ቀናት በሚኒሦታ ክፍለ ግዛት መንትዮቹ ከተሞች (ሴንት ፖል እና ሚኒያፖሊስ) የነበረኝ አገልግሎት አቅጣጫ ቀያሪ ነበር። ለሥራ መፈታቴን አመላክቷልና። ከአንጋፋው ሰባኬ ወንጌል ቄስ በልዕና ሣርካ ጋር ያገጣጠመኝ ይኸው የወንጌል ስርጭት ኮንፍራንስ በብዙ መልኩ ፍሬያማ ነበር። እግረ መንገዴንም ከሁሉም ይገዝፋል የሚባለውን “ሞል ኦፍ አሜሪካ” በከፊል መጎብኘት ችያለሁ።
ክፍል አንድ የሕይወት ታሪኬን ሳሳትም ብሎም ነሐሴ 7 ቀን 2013 (..) ሳስመርቅ ጉዳዩ የሦስቱ ክፍለ ግዛቶች ማለትም ዲስትሪክት ኦቭ ኮሎምቢያ፣ ሜሪላንድና ቨርጂኒያ አበሾች መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። መቼም በአገራችን ታሪክ አምሳ ዓመት ያልሞላው ሰው ደፍሮ ታሪኩን ሲጽፈው አልታየም። ለነገሩ አንድ አንባቢ እንዳለኝ እንኳን ሊጽፈው ገና መቼ መኖር ጀመረና?
በአስራ አንድ ወሩ ደግሞ እነሆ በንጉሡ ጸጋ ሌላ ሪኮርድ በርኩ። ሐምሌ አንድ ላይ የሦስትዮሽ መጻሕፍት ምረቃ ማካሄዴ የዓመቱ ታላቅ ክንውን ነው ማለት ይቻላል። በዚሁ ፕሮግራም ላይ ከተናገርኩት ውስጥ “በአገራችን የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ከአንድ ጸሐፊ ጓዳ ሦስት መጻሕፍት በአንድ ጊዜ ተዘጋጅተው፣ ታትመውና ተመርቀው አያውቁም። ይህ ዓይነቱ ክንውን አልታየም፤ አልተሰማም። ስለዚህ ይህ ዝግጅት በየተኛውም መለኪያ ጥቂቶች የታደሙበት ታላቅ ድግስ ነው” የሚል ይገኝበታል። ይህ ሁሉን ስለሚገልጠው ተጨማሪ ሐተታ አያሻም።
በርካታ ወዳጆቼና የሙያ ባልደረቦቼ ይልቁንም ተጋባዥ እንግዶች በሥርዓቱ ላይ ቢገኙም ከቦስተን ድረስ በመምጣት ሪኮርዱን የሰበረው ግን የመቶ አለቃ በላይነህ ዲንሣሞ ነው። ለነገሩ እርሱ ሪኮርድ መስበር ዱሮም ያውቅበታል። ሰው ቢረሳ ሮተርዳም ይህንን አትረሳም። ልጆቼ ርብቃና ኤፍሬምም ሬኮርደርና ክላርኔት በመጫወት ዝግጅቱን ውበት ጨምረውለታል።
 ሐምሌ መጨረሻ ላይ ለሁለት ቀናት ወደንግሥቲቱ ከተማ (ሻርለት) ተሻግሬ ማገልገሌና መገልገሌ ሌላው ስኬት ነው። በአንድ ቀን ምሽት አዲስ ሕይወት ቤ/ክ ውስጥ መስበክ ስጨርስ ደግሞ ወደሌላ ክንፍራንስ ተወስጄ ስለመጽሐፎቼ መናገር ችያለሁ። በሚቀጥለው ቀን ደግሞ ጧት ከጸሓፍት ጋር ተወያይቼ ከሰዓት በኋላ ደግሞ የቢሊ ግራሃምን ቤተ መጻሕፍት ጎብኝቼ ሳበቃ ማምሻውን በርሬ ወደምኖርበት አስፐን ሒል መመለስ ችያለሁ።
ከሚኒሦታ እንደተመለስኩ ስፕሪንግፊልድ ላይ በተካሄደ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ከቤሪያ አስተባባሪዎች ጋር ጠንካራ ወዳጅነት ለመመስረት በቅቻለሁ። ያም በአራት ወራት ውስጥ አፍርቶ በስልክ መስመራቸው ላይ ተከታታይ ትምህርት ለማቅረብ በሩ ይከፈትልኝ ዘንድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። በዚሁም መሠረት ከጥቅምት ሃያ አንድ ጀምሮ ለስምንት ተከታታይ ሳምንታት ያህል “ጥበብን ፍለጋ” በሚል ርዕስ በመቶዎች ለሚቆጠሩት ታዳሚዎች ጠቃሚ አሳቦችን በብዙ ደስታ አካፍያለሁ።  ምናልባትም በአዲሱ ዓመት እልባት እናበጅለት ይሆናል። (ሻርለት ደርሼ የመጣሁትም በመሃሉ ነው።)
በነዚህ ሁሉ የረዳኝን ጌታ አመሰግናለሁ። ሁሉ ነገር ግን የጫጉላ ሽርሽር ነበር ማለት አይደለም። በተለይ በጤና ረገድ ጥቂት ውጣ ውረዶች ነበሩብኝ። ከሁሉ የከበደው ግን በዚሁ ባሳለፍነው ሳምንት መኪናዬን እየነዳሁ ሄጄ ከሠላሳ ስድስት ዓመታት በኋላ ሆስፒታል መተኛቴና ከአስር ዓመት በኋላ ፀረ ተኅዋስ መድኃኒት መውሰዴ በሦስተኛው ቀን ደግሞ  “ገናን ከቤተሰብህ ጋር ለማክበር ብቁ ነህ” ተብዬ መሰናበቴ ነው።
በመጨረሻም እነዚህ ሁሉ ሰፋ ባለ መልኩ በማሳታወሻዬ ስለሰፈሩ ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም ወደፊት አንድ መድብል ሊወጣቸው ይችላል።    

ድንቅ ዓመት !

No comments:

Post a Comment