ጆናታን ጎፎርት በ1897 ዓ.ም. የቻርልስ ፊኒን የሕይወት ታሪክ ያዘለ ጹሑፍ በማንበቡ ነበር ልቡ ለመንፈሳዊ መነቃቃት የተነሣሣው፡፡ ከዚያ በመንደርደር በጸሎት ሕይወቱ ላይ መታዘዝን አከለ፡፡ ከዚያም በኋላ ለአገልግሎት በተዘዋወረበት ሁሉ የእግዚአብሔርን ክንድ ማየት ችሏል፡፡ በብዙ መቶ የሚቆጠሩና ምዕመንና አገልጋዮች በአደባባይ በደላቸውን ተናዘዙ፡፡ መነቃቃቱም ቀጠለ፡፡
ሎንግፌሎው ከቀደሙት ቅዱሳን የሕይወት ውሎ በመማር ልንበረታታ እንደምንችል ሲያብራራ እንዲህ ይላል፡፡ "የታላላቆቻችን ታሪክ እንዴት በጊዜ አሸዋ ላይ የማይጠፋን ኮቴ እያኖርን ማለፍ እንደምንችል ያስተምረናል፡፡ ይህም ጊዜያችን የእኛ እንዳልሆነ በመገንዘብ ነው፡፡"
"እንደ ጂ ካምፕቤል ሞርጋን እና ኤች.ኤ..አይረንሳይድ የመሳሰሉ ታላላቅ የእግዚአብሔር ሰዎች ትምህርት ቤት ገብተው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ለመውሰድ ዕድል አላገኙም፡፡ ዳሩ ግን ጊዜያቸውን በጥናት በማሳለፍና ያጠኑትንም በማሰላሰል በጸሎትም በመትጋት ጥልቅ ምሥጢሮችን የተረዱ የቃሉ ተማሪዎች ነበሩ" የሚለው ደግሞ የታዋቂው መጋቢና ጸሐፊ ዶ/ር ዋረን ደብልዩ ዌርዝቢ አንደኛው መጽሐፍ ነው፡፡ እንደ እኛ አምነው ከመዳናቸው ባሻገር የነዚህ ሰዎች ብርታት ምሥጢሩ ምንድነው? ታሪካቸውን ማንበብና ከውስጡ መፈልቀቅ ይቻላል፡፡ በቻይና የወንጌል መልዕክተኛ የነበረውና በዚሁ ርዕስ-ጉዳይ ዙሪያ የራሱን ጊዜ የወሰደው እንግሊዛዊው ሀድሰን ቴይለር "ታላላቅ የሚባሉት የእግዚአብሔር ሰዎች ሁሉ ድካም የነበረባቸው ቢሆንም ለእርሱ ብዙ የሠሩት አብሮአቸው መኖሩን ስለተቀበሉ ነው" ወደሚል መደምደሚያ አምርቷል፡፡
ሉዊስ ፓላው የተሰኘ የወንጌል ስርጭት ቡድን መሪ ደግሞ "ሁሉ ክርስቲያን የሙዲን ታሪክ ማንበብ አለበት፡፡ እኔ ራሴ ግማሽ ደርዘን ጊዜ አንብቤዋለሁ፡፡ ለምን ቢሉ እግዚአብሔር እንደዚህ ባሉ ተራ ሰዎች ተጠቅሞ የሠራውን ድንቅ ካነበበ በኋላ የማይነቃቃና የማይባረክ ሰው የለም" ብሏል፡፡
(እነማን ነበሩ ከሚለው መጽሓፌ መግቢያ የተወሰደ)
No comments:
Post a Comment