ማን ብለን እናስታውስህ?
ዓለማየሁ ማሞ የሚለው ስሜ አሁንም አልተቀየረም። ደራሲና ጋዜጠኛ ነኝ። ያ ካልበቃም ገጣሚና ተርጓሚ የሚለውን ማከል ይቻላል።
አሜሪካ በሚሉት አገር ሜሪላንድ ክፍለ ግዛት አስፐን ሒል ከተሰኘች ከተማ እኖራለሁ።
የአንተ መጻሕፍት በመደርደሪያዎች ላይ ከታዩ ዓመታት ተቆጠሩ። መጻፍ አቆምክ እንዴ?
ልክ ነው። አስራ አምስት ዓመታት ነጎዱ። ምክንያቱ ከትውልድ አገሬ 10000 ማይሎች ርቄ መኖሬ ነው። መጻፍ እንኳ ጨመርኩ
እንጂ አላቆምኩም። ግን መጻሕፍቱን አዲስ አበባ ላይ ለማሳተም ሁነኛ ሰው አልነበረኝም። ሁነኛ ያልኩት ሰው የገንዘብ አያያዙ ጠፍቶበት
ዐይቼ ተሳቀቅሁና ለዓመታት ሸሸሁ። በዚያ ላይ አስባታሊው የኑሮ ዘይቤ ፋታ አልሰጠኝም። ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት መሆኔ፤
እስከ አርባ ሰዓቶች በሳምንት መሥራቴና ትምህርት ቤት መሄዴ በቀን ጥቂት ሰዓቶች የሚበቁት አይደለም። ይሄ ሁሉ አንሦ አሁንም መጻፌ
ራሱ እንደተአምር መቆጠር አለበት።
በርግጥም ርቀህ ቆይተሃል። እና የጻፍካቸው በሙሉ ለመታተም ጊዜ እየጠበቁ ነው ማለት ነው?
ለነገሩ ጥቂት ጥቂት እያደረግሁ ሚሽጋን ላይ አሳትሜአቸዋለሁ። ግን ያገኟቸው በሰሜን አሜሪካ ውሱን ክፍለ ግዛቶች የሚኖሩና
አውሮፓ ያሉ አንባብያን ናቸው። የላክሁላቸውና በ2011 ለጉብኝት
የመጣሁ ጊዜ እጃቸው ላይ ያኖርኩላቸው ጥቂት የአዲስ አበባ ወዳጆቼ ብቻ መጻሕፍቱን ነክተዋቸዋል። ነጋ ጠባ የመረቀኝ አንባቢ ግን
አላያቸውም።
በውሱን ክፍለ ግዛቶች አልክ? በሠለጠነው ዓለም መላውን አሜሪካ እንኳን ማዳረስ አልቻልክም?
አዎን ከአምሳዎቹ ክፍለ ግዛቶች ውስጥ ሃያውን ብቻ ነው በብዙም ይሁን በጥቂቱ የነካኋቸው። ለምን ወደሚለው ከገባን በመጀመሪያ
በሁሉም ክፍለ ግዛቶች ውስጥ አበሻ አለ ማለት አይቻልም። በዚያ ላይ ሰዶ ማሳደድ አልወድም። አገሬን ለቅቄ የሄድኩበትን ምክንያቶች
ሳስብ አንዱና ትልቁ እርሱ ነው። አዎን አንዱ የመጻሕፍት ገንዘብ ስብሰባ ያመጣብኝ መከራ ነው። በተለይ ባለመዝሙር ቤቶች ነን ይሉ
የነበሩትን ጥቂት ቁጭ በሉዎች መታገሥ አልሆነልኝም። ቁጭ ብዬ ልጻፍ ወይስ እነርሱ ዘንድ ልመላለስ? የእምነትና የመጻፍ መብት በተከበረባት
አገር መኖሬ የቆመው በዚህና ሌሎች ምክንያቶች መሆኑን ሳስብ አሁንም እቆዝማለሁ። ወደ”ተስፋይቱ ምድር” ከመጣሁም በኋላ እነዚያው
ሰዎች ቀድመውኝ ውቅያኖስ አቋርጠውና ተደላድለው አገኘኋቸው። ግን ምን አማራጭ ነበረኝ? ከዚህ ወዴት ልሂድ? በቆይታዬ አሜሪካ የገቡ
እንጂ አሜሪካ ያልገባቻቸው ጥቂት እንዳይደሉ ተረድቻለሁ። ከዚህን የተነሣ ጥቂት የማይባሉና መንፈሱ የላላ ሰው ካገኙ ለሕመም የሚዳርጉ
ገጠመኞች አሉኝ።
ከነዚያ ዋና የምትላቸው የትኞቹን ነው?
እንግዲያው ሦስት ቦታዎች ላይ የገጠመኝን ላውሳ። በ2005 ዓ.ም ሦስቱን ኩታ ገጠም ክፍለ ግዛቶች ማለትም ሜሪላንድ፤ ዲሲና ቨርጂኒያን ያማክላሉ
ባልኳቸው ሦስት መደብሮች በወቅቱ ያሳተምኩትን መጽሐፍ ለሽያጭ አስቀምጬ ነበር። በነገራችን ላይ ውሉ በሚሸጡት መጻሕፍት ልክ ለእነርሱ
ድርሻቸውን ማካፈልን ይጨምራል። ስለዚህ ተጨማሪ ንግድ እንጂ በጎ አድራጎት አይደለም። በዚያው ሰሞን ከመስታወት ሬዲዮ አዘጋጅ ጋር
ቃለ ምልልስ አድርጌ ነበር። በዚያም ግለት ታግዞ መጽሐፉ ፈጥኖ ተሸጠና አለቀ። ገንዘቡን ለመሰብሰብ ስሞክር ግን ፈገግ የሚያሰኙና የሚያስቆዝሙ ነገሮች አጋጠሙኝ።
መጀመሪያ የሄድኩት
ዘጠነኛውና ዩ መንገዶች መጋጠሚያ ላይ ነበር። “ባለቤቱ የለም” ብለው አሰናበቱኝ። ይህኔ እኒያ ባለመዝሙር ቤቶች ትዝ አሉኝ። ከላይ
እንዳልኩት ከአገሬ ለመውጣት ውሳኔ ላይ ካደረሱኝ በርካታ ምክንያቶች የአንዱ ፈጣሪ የሆኑት ቁጭበሉዎች ሲቀበሉ የሚያሳዩት ፈገግታ ብር አምጡ ሲባሉ ይጨልም ነበር።
ሁለተኛው ደግሞ
ስንት መጽሐፍ እንዳስቀመጥኩ እኔኑ መልሶ ጠየቀኝ። አሜሪካ የሚኖር ነጋዴ የተረከበውን ቁራጭ ወረቀት ላይ አለመጻፉ ቢያሳዝነኝም
ሃያ መሆኑን ነገርኩት። “ወዳጄ እኛ ከደራሲያን የምንቀበለው አምስት መጽሐፍ ብቻ ነው። በጣም ከበዛ አስር። ለምን ቢባል የኛ ሰው
አያነብም። በል የአስር መጽሐፍ ዋጋ በቼክ ጽፌ አስቀምጥልሃለሁ” አለና መልሴን ሳይሰማ ስልኩን ዘጋ። ሰማንያ በመቶውን ለራሱ አስቀረ
ማለት ነው።
ከሁሉ አስገራሚው
ሜሪላንድ የገጠመኝ ነው። ወደ መደብሩ ስሄድ አንዲት እናት ተቀምጠዋል። እንዲህ ዓይነት ዕድሜ ላይ ያሉ እናቶች ብዙ ጊዜ ሞግዚቶች
ናቸው እንጂ መደብር ውስጥ አይቀመጡም። ከተቀመጡበት የማይነቃነቁት ሴትዮ ታዲያ ዋጋ ስለማያውቁ አንድ ነገር ሲጠየቁ ስልክ ይመቱና
ከባለቤቲቱ ይጠይቃሉ። በወጣትነታችው አራዳ እንደነበሩ ለመገመት ሞከርኩና ተውኩት። ግን ሰላምታ አቅርቤ ትንሽ ካዋራኋቸው በኋላ
ስለራሴ መጽሐፍ እንደገዢ ጥያቄ አቀረብኩ። አለመኖሩን ነገሩኝ። በጣም እንደምፈልገው አሳስቤ ስጠይቃቸው ምን እንዳሉኝ ታውቃለህ?
“ደራሲው ፈላጊ እንደሌልው ስላወቀ ሰብስቦ ወስዶታል!”። ደራሲው እኔ መሆኑን ገልጬ ባፋጥጣቸውም መልሰው ልቤን አደረቁኝ እንጂ
አሮጊቷ አልደነገጡም።
እነዚህን ገጠመኞች
ዘጠኝ ዓመት ሙሉ ስቄ ለመሳቂያ አድርጌአቸዋለሁ። አንዱ የመጻፍ ለዛ የደረሱብንን ክፉ ነገሮች ስንቀልድባችው የሚንጠፈጠፈው ወዘና
ነው። በጥቅሉ ግን ጥቂት የማይባሉ ሰዎች እዚህ ሲመጡ ከመሻሻል ይልቅ ብሶባቸዋል።
የሰዓትን አከባበርን ነገርማ እንተወው።
አንስተኸዋልና ባንተወው። ይልቅ ስለሰዓት አከባበር ምን ታዘብክ?
አንድ የፌስቡክ
ወዳጄ ለጥፎት ዐይቼ ባሳቀኝ አባባል ልጀምር። ስለእኛ ቀጠሮ ነው። “ከ5-6 እመጣለሁ፤ ከ7-8 ዐይተኸኝ ካልመጣሁ ከ9-10 ሂድ”
ይላል። ከመጋነኑ በስተቀር ውሸት ነው ብሎ የሚከራከር የለም። መጽሓፍ በኪሴ ይዤ “ባለቀጠሮዎች” እስኪመጡ መጠበቅ ዕድል ፈንታዬ
ነበር። ከቀኑ ሰባት ሰዓት የሚጀምር አንድ ስብሰባ ላይ እንድናገር ተጋብዤ ዘጠኝ ተኩል ላይ ነው መድረኩ የተሰጠኝ። ወሬዬን አሳጥሬ
ወደሚቀጥለው ፕሮግራም ለመሄድ ከመድረክ በቀጥታ ወደመኪናዬ ተወነጨፍኩ። እአሁን አሁን ግን የቅርብ ወዳጆቼም ተመሳሳይ አቋም ይዘዋልና አብረን መቋቋም ጀመረናል።
በሦስትዮሹ የመጻሕፍት ምረቃ ላይም የማይረሳ ሌላ ታሪክ ሠርቻለሁ።
ምን አደረግህ?
ፕሮግራም ስምንት
ሰዓት ተኩል ነበር የታቀደው። ከተጋባዥ መቶ እንግዶች ከሩብ ሲል ሦስት ሰዎች መጡ። በተባለው ሰዓት የደረሱልን ከሃያ የማያንሡ ከሠላሳ የማይበልጡ እንግዶቼ
ብቻ ነበሩ። ሁሉም እንዲቀመጡ ካደረግሁ በኋላ ድምፅ ማጉያውን ጨበጥኩ። እንኳን ደህና መጣችሁ ካልኩ በሁዋላ በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ
ላይ አንዲህ አልኩ። “ግብዣው የእኔ ነውና አክብራችሁ ስለመጣችሁ አመሰግናለሁ፤ አሁን ፕሮግራሙን እነሆ ጀመርኩት። የእኛ ሰው ሰዓት
አያከብርም እያለን በየመድረኩ ብዙ ተናግረናል፤ እኔና ወዳጆቼም ጽፈናል። የማርፈዱ ጣጣ ምክንያተ ብዙ ቢሆንም አንድ ያላስተዋልነውን
ሰበብ ዛሬ ልንገራችሁና ንግግሬን ልጀምር። እንደ እናንተ ያሉ ሰዓት አክባሪዎች ቀድመው ይደርሳሉ። እንደ እኔ አይነቱ ደጋሽ ደግሞ
አዳራሹ ሞላ እስኪልልለት ሻይ ቡና እንበል እያለ ያጉላላችኋል። በሚቀጥለው ጊዜ ታዲያ እናንተም አርፋጆች ትሆናላችሁ። እኔ ይህንን
አልደግፍም። እነሆ ጀምሬአለሁ! ተንጠባጥበው የሚመጡት ይምጡ። ይህም ብቻ ሳይሆን ፕሮግራሙን በመርሃ ግብሩ መሠረት በሰዓቱ እዘጋዋለሁ።”
አደረግሁት። አንድ የሬዲዮ አዘጋጅ ወዳጄ እንደነገረኝ በበነጋው የከተማው ወሬ ይኸው ነበር።
አሁን ምን እያሰብክ
ነው?
ለመነበብ የማልፈነቅለው
ድንጋይ የለም። ምን እያሰብክ ነው ስባል መልሴ የበለጠ ለመሥራት ነው። የስርጭት አድማሴን ለማስፋት ነው። ከምንም ይልቅ እንደመንፈሳዊ
ሰው ሳሰላስል ወደ አገሬ የምመለስበት ጊዜ አሁን እንደሆነ ጠንክሮ ይሰማኛል።
መቼ ነው የምትመለሰው?
መመለስ የሚለውን
ቃል በመደበኛ ትርጉሙ አይደለም የተጠቀምኩበት። መመላለስ የሚችል ሰው ስለመመለስ ለማሰብ መቸኮል አይገባውም። በፈለግሁ ጊዜ መምጣት
እችላለሁ። እንዲያውም ፋይዳ ያለው ነገር በአገሬ ውስጥ ለመሥራት (በኢንቨስትመንት ፣ በበጎ አድራጎት ወይም ሌላ) እያወጣሁና እያወረድኩ
ነው። ዛሬ ግን መመለስ ስል ስለእኔነቴ ሳይሆን ስለሥራዎቼ እያወራሁ ነው። በውጭ ቆይታዬ አስራ አንድ መጻሕፍትን አሳትሜአለሁ።
ቀደም ብዬ እንዳነሣሁት ሁሉም የተነበቡት በሰሜን አሜሪካና አውሮፓ
ነው። እናም በየተራ አገር ቤት እንዲታተሙ አስባለሁ። መመለስ ይህ ነው። ሥራዎቼ ለወገኔ መድረስ አለባቸው። የእስካሁኑ ሙከራ ከምንም
ቢሻልም ውቅያኖሱን ትቶ ኩሬ ውስጥ ከመቦጫረቅ የተለየ አልነበረም። አገሬ የምመለስበት ጊዜ አሁን ነው። አዎን መመለሻዬ ደርሷል!
አሁን ታዲያ እጅህ ከምን?
በያዝነው የአውሮፓውያን ዓመት ቢያንስ ሦስት መጻሕፍት እንዲታተሙና እንዲሠራጩ ፍላጎቱና ዝግጁነቱ አለ። አሳቤን ካልቀየርኩ
በስተቀር ክፍል አንድ የሕይወት ታሪኬና የማዕበል መንገደኞች የሚለው መጽሓፍ ይህንን ዕድል ሳያገኙ አይቀሩም። ለጊዜው ግን አንድ
መጽሐፍ ደግሜ በማሳተም ሕልሜን እውን ማድረግ ጀምሬአለሁ።
የትኛውን?
የብርታቱ ምሥጢር የተሰኘውን የስሚዝ ዊግልስዎርዝ የአገልግሎት ታሪክ ደግሜ አሳትሜዋለሁ። በስርጭት ላይ ነው!!!
ለምን እርሱን መረጥክ?
በሁለት ምክንያቶች ነው። አስራ አምስት ዓመታትን ተሰውሬ ብቅ ስል አዲሶቹን ሥራዎቼን ይዤ ከምመጣ ይልቅ ቢያንስ በሚታወቀው
መጀመሩ ያዋጣል። አዲሱ ትውልድ ማንነቴን ቢጠይቅ እንኳ ነባሮቹም አላለፉምና ዓለማየሁ ማን እንደሆነ ይነግሩታል። ሌላው ምክንያት
ደግሞ ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት ያለማቋረጥ ሲጠየቅ የነበረ መጽሓፍ ስለነበረ ነው። በ2011 (እ.አ.አ ) ለጉብኝት በሄድኩም
ጊዜ የሚያውቁኝ ሰዎች የጠየቁኝ ስለጤንነቴ ሳይሆን ስለዚሁ መጽሓፍ ነበር። ከሓዋርያው ጳውሎስ ቀጥሎ እግዚአብሔር በኃይል ተጠቅሞበታል
የሚባለውን ይህን የእግዚአብሔር አገልጋይ ታሪክ በማንበብ ብዙዎች ተባርከዋል። በርግጥም ያ መጽሓፍ ብዙዎችን ነክቷል።
ብዙዎችን ነክቷል ያልከውን እስኪ በምሳሌ አብራራልን?
ገና አገር ቤት እያለሁ የስርጭቱ ፍጥነት የመጽሓፉን ተወዳጅነት ያጎላ ነበር። ያነበቡትም ብዙ እንደተጠቀሙበት በአካልም
በጽሑፍም ነገረውኛል። በተለይ ከዝዋይ ማረሚያ ቤት የደረሰኝ ደብዳቤ መቼውንም የምረሳው አይደለም። “መጽሐፉን እግኝቼ በማንበቤ
በሕይወቴ ትልቅ መነቃቃት ሆኖአል። በአንድ ወቅት አማኝ ነበር። ግን በመሐሉ ልቤ ከጽድቅ ተንሸራተተና በድካም ስመላለስ ወንጀል
ፈጽሜ ነው የታሠርኩት። አሁን ጌታ ከዚህ እንዲያወጣኝና እድሜ ልኬን እንዳገለግለው እየጸለይኩ ነው” የሚል ነበር። ወደአሜሪካ ከመጣሁም
በኋላ ብዙዎች ስለመጽሐፉ ወሬ እንደሰሙ ግን ለማግኘት እንዳልቻሉ አንስተውብኛል። አንደኛ ሚዜዬን ጨምሮ በርካቶችም አገር ቤት እንዳነበቡትና
እንደጠቀማቸው ነገረውኛል።
በቀደም ዕለት እንኳ ለአገልግሎት የጋበዘችኝ መጋቢ ለጉባዔው ስታስተዋውቀኝ እንዲህ ብላ ነበር። “ከዓመታት በፊት አንድ
መጽሓፍ አንብቤ ሕይወቴ ተቀይሯል። ያንን ከቧንቧ ጠጋኝነት እስከታላቅ የእግዚአብሔር አገልግሎት የተሰኘ መጽሐፍ የተረጎመው ወንድማችን
ዛሬ የእግዚአብሔርን ቃል ያካፍለናል”። ምስክርነቶቹ ብዙ ናቸው፤ ግን ጥቂቶቹን ተናገርኩ።
እንኳን ደህና ተመለስክ እንበልህ?
እንኳን ደህና ቆያችሁኝ ለማለት አላመነታም!