Thursday, September 12, 2013

በዚህ ወገን

እንኳን ተጨልጦ
እንኳን ተገልብጦ
ጠብታው እሚያሰክር
እሚያዞር ጥንቢራ
እግዜር ጠመቅሁ ይበል
ኑሮ ይሉት ቢራ
(ሞገስ ሃብቱ)
********************
ኑሮ ይሉት ቢራ
እግዜር ከጠመቀው፤
ተጠቦና አቅዶ
እጅግ አጣፍጦ ነው።
አሁን ቃናው ጠፍቶ
ጥንቢራ ማዞሩ፤
አጠጣጡ ጠፍቶን
ከኛው ነው ችግሩ!

(ዓለማየሁ ማሞ)

Thursday, August 15, 2013

ለማሳወቅ ያህል


በበርካታ መጻሕፍት ዝግጅት ሥራ ላይ የመሳተፍ አስደሳች ዕድል ገጥሞኛል። ጽፌአለሁ፡ ገጥሜአለሁ፤ ተርጉሜአለሁ፡ እንዲሁም አርሜአለሁ። አሁን ደግሞ ይኸው የታሪኬን ፈርጦች ጻፍኩ። ከነዚያ መሃል የሕትመት ብርሃን ያዩና አንባቢያን እጅ የገቡ ከሠላሳ በዋል። በዚህች በመጨረሻዋ ገጽ ሲሦዎቹን ልዘርዝር...

ድርሰትና ዝግጅት

1)  ኑሮ በአሜሪካ
2) ልጆችን ወደእውነት መምራት
3) እነማን ነበሩ?
4) የማዕበል መንገደኞች

ትርጉም

5) የወጣትነት ጥያቄዎች
6) የብርታቱ ምሥጢር

አርትዖትና እርማት

7) ሾተልና መስቀል
8) የጋብቻ እንቆቅልሽ

ግጥም

9) የዘመኑ ሰው
10) ለተሰጠኝ ዕድሜ

Thursday, August 1, 2013

ይድረስ ለወዳጆቼ

 
የሕይወቴ ፈርጦች “ከቀበና እስከ አስራ አራተኛው ጎዳና” የተሰኘውን መጽሓፌን ረቂቅ ጽፌ ጨረስኩ። ይኸውም ጎላ ያሉትን የሕይወት ገጠመኞቼን ያካተተ ክፍል አንድ ስብስብ ነው። ሁሉን አስታውሻለሁ ብዬ ግን አልገምትም። ስለዚህ በቀበና አንደኛ ደረጃና በኮከበ ጽባሕ አጠቃላይ አብራችሁኝ ለተማራችሁ በቀድሞው የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል የሥልጠና ማዕከል ከእኔ ጋር ለነበራችሁ በፍሪጌት 1616 ላይ በመርከበኝነት ለሠራችሁ፤ በመደቡ ሆስፒታል አብራችሁኝ ላከማችሁ፤ የምጽዋን ምጥ ፅዋ ለተቃመሳችሁ ኋላም በጋዜጠኝነትና በድርሰት ሥራ ከጎኔ ለተጠመዳችሁ ወዳጆቼ መልእክት አለኝ። ትዝ እሚላችሁን የጋራ ገጠመኛችንን ላኩልኝ ወይም አስታውሱኝ። ሚዛን ከደፋ መጽሓፉ ውስጥ አካትተዋለሁ። ለጥረታችሁም ዕውቅና እሰጣለሁ።
በሺሕ የምትቆጠሩት የፌስቡክ ወዳጆቼ ደግሞ ይህንን መልእክት “ሼር በማድረግ” ለብዙዎች እንዲደርስ እንድታደርጉ አደራ እላለሁ።
መልካም ቀን!
ዓለማየሁ ማሞ
በነገራችን ላይ ማንነታቸውን ለመደበቅ የቀየርኳቸውን ሳይጨምር በመጽሐፉ ውስጥ የተነሡ ስሞች በቅደም ተከተል እነዚህ ናቸው።
ወይዘሮ የሺ ዓሊ
ፍቅር(ተ) ታደሠ
ርብቃ ዓለማየሁ
ኤፍሬም ዓለማየሁ
መምህር አጥናፉ
መምህር ጌታቸው
አባ አዳነ
ምክትል ርዕሰ መምህር ተረፈ
ዘውዱ ከበደ
እሸቱ
ብርሃኑ ትርፌ
መንገሻ ዮሐንስ
ሰለሞን ዮሐንስ
አበበ ዮሐንስ
ሰለሞን ተስፋዬ
መሠረት ዘለቀ
መምህር ዘውዴ ጥላሁን
አዲስ
ተክለማርያም
መምህር ግላሤ
መምህር ማናለብሽ ግዛው
ዘካርያስ ለማ
ጴጥሮስ ለማ
አምሳ አለቃ ከበደ ኃይለኛው
ምንይልክ ሰለሞን
ወንድማገኝ ጎርፉ
ጌታነህ ኃ/ጊዮርጊስ
ሙሉጌታ ወልደየስ
ዳንኤል በቀለ
መምህር ማሞ
ዓለሙ
ያሬድ ከበደ
የሺመቤት
ቤዛኩሉ አጥናፉ
አቶ ኃይሉ ጽጌ
ማማዬ በጋሻው
ገነት መኩሪያ
መስፍን
የአስር አለቃ ወርቁ ሰይፉ
ወታደር ታደመ ዓሊ
መምህር ታደሠ ዘውዴ
እስክንድር ተሰማ
ሲሳይ ወርቁ
ማ/ዋ/ኦፊሰር ብዙነህ ገ/ሕይወት
በፍርዱ ወርቁ
ኤብል ሲማን ሓድጉ ጥሩነህ
ጁኒየር ሌፍተናንት ወርቁ
ኮማንደር ተ/ኃይማኖት ገ/ማ
ነጋሽ ቶሎሣ
ወርቁ ገብሬ
ግዛቸው ኃይለኢየሱስ
አዳነ ነመራ
ጎሣ ኃይሌ
ሉሉ ቢልልኝ
ዘነበ ወላ
በላይ
ማቴዎስ (ማቹ)
ጁ/ሌ ዓለማየሁ ገሮ
ይመር ዓሊ
አብዱልቃድር አደም
ፒ/ኦ አፈወርቅ ቤዛ
ኤልያስ ስለሺ
ሰለሞን የሺዳኛ
ሲሳይ ንጉሡ
ኃይሌ ግርማይ
ገዛኸኝ ተስፋዬ
ፒ/ኦ ኃይሉ ገ/ጻድቅ
ዶ/ር መንግሥቱ ይልማ
ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን
አክሊሉ ምትኬ
ንጉሤ ሲሣይ
ዓለምነህ ወርቁ
ወንድሜነህ ግርማይ
የኋላሸት ሣሕሌ
መላኩ ሙላት
ወጋየሁ
ነቢዩ ሸንኮሬ
ዮሓንስ
ዶክተር ወርቁ
ዶክተር ጋሊያ
አበራ (ጤና ረዳት)
ቤተልሔም ዕንቁሥላሴ
በዛወርቅ (ሜቲዎሮሎጂስት)
ኃይሉ ቦንገር
ብርሃኔ የሱፍ
ያሬድ ሣሕሉ
እንትዋን በርሔ
ሙዚቀኛው ፍቅሬ
ታደሠ ጎንፋ
ሌፍተናንት መኩሪያ ዲዲማ
ብሔራዊ ወታደር ፀጋዬ
ተናኘ አበራ
ዮሴፍ ገዳሙ
ተቋመ ነጋሽ
ከፍያለው ይግዛው
ያዕቆብ(ቺሚ)
ከምሱር ከበደ
ሣልልህ ምሕረት
አደራ ባዬ
መ/አ ኃይሉ አበበ
ማርታ
አሳብነህ መለሠ
ፍሬገነት
ወንጌላዊ ስንታየሁ መንግሥቴ
ተስፋዬነሽ ከበደ
ዓለምፀሓይ ከበደ
ሱራፌል አንበሉ
አቻምየለህ በጋሻው
ምትኩ ማሞ
ዓለማየሁ ወልደገብርዔል
ሣራና ብርቱካን
ሸዋዬ ደጋጋ
ደረጄ አበበ
ስመኝ ግዛው
ቤተልሔም ክፍሌ
ፀጋዬ ኃይሉ ብሩ
ሞገስ በርይሁን
ዘውዲቱ ጥላሁን
ደምሴ ፅጌ
ሐዲስ እንግዳ
ከድሮ አደም
ፀሓይ (ፎቶግራፈር)
መስፍን ሃብተማርያም
መንግሥቱ አበበ
ክፍሌ ወርቁ
ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ
ቀኛዝማች መልኬ ይትባረክ
ዮዲት (ላይብረሪያን)
መኮንን (የበረራ ትራፊክ)
አክሊሉ ልደቱ
አምባሳደር ካሳሁን አየለ
ግርማ ለማ
ገበየሁ ዋለልኝ
ስምረት ደመረ
ዓለም ይርጋ
ፍቅረየሱስ ሁንዴሣ
አዲሴ አማዶ
ምንይልክ ታምራት
ደረጄ በጋሻው
ወርቅነህ ደርቤ
ገዛኸኝ አንበሉ
ዐወቀ ደጋጋ
ራይንሃርድ ቦንኬ
ደምሴ በላይ
ወንድም ታዬ (አዋሳ)
ፕሮፌሰር ዝናቡ ገ/ማርያም
ታፈሰ ክፍሌ
ደረጄ በላይነህ
ፒተር ባንደርበርግ
ዳኜ አበራ
መስፍን
ብርሃኔ ዘለቀ
ስንዱ ኃይሌ
ብርሃኑ አሰፋ
ቢንያም ንጉሤ
ዓለምነህ ዋሴ
ንጉሤ አክሊሉ
ተስፋዬ ገብረአብ
ንጉሤ ቡልቻ
ዓለማየሁ በቀለ
ሩት አንድና ሁለት
ጋሼ ሚናስ ብሩክ
መምህርት ፀሓይ ታችበሌ
አልማዝ ታችበሌ
ኪሩቤል ጸጋዬ
ደራሲ ጌታቸው በለጠ
ዘነበ ገብረሓና
እሸቱ
መንግሥቱ
ፓስተር መርዕድ ለማ
ካሣዬ ኃይሌ
አባይነህ ወ/ጊዮርጊስ
ተሾመ ብርሃኑ
ጄኒፈር ፓርሜለ
አይሸሹም መኮንን
ሸዋዬ ማሞ
ታምሩ ገዳ
ፈቃዱ በሻህ
ጂግሣ አበበ
ወንጌላዊ ተቀባ
ብዙአየሁ አበበ
ብዙነሽ ቅጣው
አንተነህ ገ/ማርያም

Monday, July 29, 2013

የሁለቱ ነገሥታት ልደት


ሰሞኑን ዋነኛው ወሬ ወንድ ልጅ ተወለደ አዲስ ንጉሥ ወደ ምድር መጣ የሚል ሆኖ ነው የሰነበተው። ይባስ ብሎ ልጁ የተወለደው የቢቢሲ መቀመጫ ከሆነው እንግሊዝ አገር ሆነና የዜና ሁሉ ቁንጮ ሆኖ አረፈ። ግን እኮ ከ2000 ዓመታት በፊትም እንዲሁ በምድራችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተባለ ሌላ ንጉሥ ተወልዶ ነበር። እናም የሁለቱን ነገሥታት ልደት ለማነፃፀር ወደድኩ። ለዚያ የገፋኝ የመጀመሪያ አሳብ የተወለዱበት ሥፍራ ነው። እንደሰማነው የእንግሊዙ አልጋ ወራሽ የተወለደው በለንደን የቅድስተ ማርያም ሆስፒታል ሲሆን ኢየሱስ ግን ዛሬ በካርታ ላይ ለማመልከት በሚቸግር በረት ውስጥ እንደተወለደ በግርግምም እንደተኛ ልብ ይሏል። በዚሁም መሠረት ኢየሱስን ታላቁ ንጉሥ የለንደኑን ሕፃን ደግሞ ትንሹ ልዑል እያልኩ እጥር ምጥን አድርጌ እንደሚከተለው ተነተንኳቸው።
ዜናው
ሓምሌ 22 ከቀኑ 10 ሰዓት ከሃያ ደቂቃ ላይ የተወለደው ሕፃን እርሱም ትንሹ ልዑል በጾታው ወንድ መሆኑን ለማብሠር የለንደንን ትልቅ መመልከቻ መንኮራኩር ጨምሮ ከተማይቱ ሁሉ በሰማያዊ ብርሃን ደምቃ አምሽታለች። ለክብሩም ስልሳ ሁለት ጊዜ መድፍ ተተኩሷል። “ሕፃን ተወልዶልናል ፤ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል” ብሎ ነቢዩ ኢሳይያስ ከአራት መቶ ዓመታት በፊት የታላቁን ንጉሥ ልደት አውጆ ነበር። በታሪክ ታይቶና ተሰምቶ በማያውቅ ሁኔታ ድንግሊቱ ፀንሳ አማኑኤልን ወለደች። ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው ይለናል የመጻሕፍት ሁሉ መጽሐፍ የሆነው ሕያው የእግዚአብሔር ቃል። ዜናውንም ወደምድር ያመጡት ጋዜጠኞች አልነበሩም። መላእክት ናቸው። ለተናቁት በግ ጠባቂዎች ይህንኑ ሲነግሩአቸው “ለምድር ሁሉ የሚሆን የምሥራች” የሚል ግሩም ርዕስ ሰጥተውታል። በዙፋኑ ዙሪያ የሚዘምሩት የእነዚሁ መላእክት ዜማ ወደሰው ልጆች ጆሮ የገባውም ያኔ ነበር።       
አቀባበል
እንግሊዝን የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዴቪድ ካሜሩን ዛሬ የታላቅ ደስታ ቀን ነው ሲሉ በይፋ ተናግረዋል።በትንሹ ልዑል መወለድ ደስ የተሰኙ ነገሥታት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትርና የካንትረበሪውን ሊቀ ጳጳስ ጨምሮ በርካቶች ከዓለም ዙሪያ የደስታ መግለጫ መልእክት አስተላልፈዋል። “ሁላችንን በአንድ የሚያሰባስብ ከዚህ የተሻለ ታሪካዊ ክስተት ከቶ የት አለ” ስትል ከሆስፒታሉ ደጃፍ ከተኮለኮሉት አንዷ በመፍነክነክ የተናገረችው የብዙዎችን ስሜት ይወክላል። የግብዣው ወጪ ብቻ 400 ሚሊዮን ፓውንድ ይገመታል ነው ያሉት የሒሣብ ዐዋቂዎች። ወደታላቁ ንጉሥ ስንመለስ ግን ጥቂት ምሥጢሩ የገባቸው ጠቢባን ስጦታ ያምጡለት ታታሪዎቹ እረኞችም በመደነቅ ይጎብኙት እንጂ መላው ዓለም ስለንጉሡ መወለድ ደንታ አልነበረውም። ከመጀመሪያውም እንኳን የማዋለጃ ሥፍራ ማደሪያም አላገኘም። ስለዚህ ከከብቶች ጋር በአንድ በረት እንደታጎር ሆኗል። እዚያው ሳለም የልደት በዓል ሳይሆን ንጉሡና ባለሥልጣናቱ ሳይዉሉና ሳያድሩ የሞት ድግሥ አዘጋጅተውለታል። በወጣትነት ዘመኑ የሦስት ዓመት ተኩል አገልግሎቱን ጨርሶ በስቅላት ቢገደልም ቅሉ ሞት የተፈረደበት ግን ገና ከመወለዱ ነበር። 
ስማቸው
ልዑል ዊልያምና ባለቤቱ ኬት ስለልጁ ስም ሲጠየቁ “እያሰብንበት ነው ፋታ ስጡን” ነበር ያሉት። ልጁ ከተወለደ በኋላ ተማክረው ያበጁትን ስም አሳውቀዋል። እናም ትንሹ ልዑል የተከበሩ ግርማዊ የኬምብሪጅ ልዑል ጆርጅ አሌክሳንደር ሊዊስ ተብሎአል።ወደታላቁ ንጉሥ ስንዞር ግን አሁንም ከመወለዱ ብዙ መቶ ዓመታት በፊት  “ስሙም ድንቅ መካር ኀያል አምላክ የዘለዓለም አባት የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል” ብሎታል ነቢዩ ኢሳይያስ። ወደእናቱ የመጣው መልአክም ስሙ ማን እንደሚሆን ተናግሮአልና ማርያምና ዮሴፍ መማከር አላስፈለጋቸውም።
ንግሥናቸው
የትንሹ ልዑል ቅድመ አያት ንግሥት ኤልሣቤጥ ለ61 ዓመታት ዙፋኑን እንደተቆናጠጡ ናቸው። አያቱ ያንን ወንበር ሲጠብቅ አረጀ። ቀጥሎ ደግሞ አባቱ አለ። ያንን ሁሉ ተከትሎ ነው አዲሱ ሕፃን በአራተኝነት ለንግሥና የተሰለፈው። ከቀናው ከእንግሊዝም አልፎ ካናዳ፤ አውስትራሊያና ጃማይካን ጨምሮ በአስራስድስቱ የኮመንዌልዝ አገሮች ላይ ንግሥናው ይጸናል።ምናልባትም ሳይነግሥ ሊሞት ይችላል። በአንፃሩ የኢየሱስ ንግሥና ከዘመናት በፊት የጸና ነው። ወደምድር ሲወርድም ንጉሥ ነበር። የገባቸው “ሆሣዕና በአርያም” ብለውና ዘንባባ አንጥፈው በሆታ ተቀብለውታል። እርሱ ንጉሥ ብቻ ሳይሆን የነገሥታት ንጉሥና የጌቶችም ጌታ ነው። የተከበሩ ንግሥት ኤልሳቤጥን እና የልጅ ልጃቸው የሆነው ትንሹን ልዑል ጨምሮ ታላላቆች ሁሉ በእግሩ ሥር ወድቀው ይሰግዳሉ።
መደምደሚያ
ቤኪንጋም ቤተመንግሥት አንድ ልዑል ተጨመረልን ተብሎ ፌስታው ቀልጧል። እንኳን ደስ ያላቸው። በጥቅሉ ግን ይህ ዓለም ከታላቁ ንጉሥ ወደ ምድር መምጣት ይልቅ በትንሹ ልዑል መወለድ የተመሰጠ ይመስላል። የታላቁን ንጉሥ ልደት ዘክር ሲባልም የራሱን ስጦታ ለመለዋወጥ ሚሊዮኖችን የሚያባክን ጥበብም የጎደለው ሆኗል። ገናን ጠብቆ ንግዱን ያጧጡፋል፤ ዳንኪራ ይመታል። ኢየሱስ ከ2000 ዓመታት በፊት በቤተልሔም ተወለደ ይላል። አንተስ ያንን ሰምተህ ዳግም ተወልደሃል ሲባል ግን ሰማይና ምድሩ ይዞርበታል።  በርግጥም የዞረበት ዓለም ነው ጃል!


Thursday, July 18, 2013

ስማችንን ያስጠሩ

 
እነሆ በሁለት ሠፈርተኞች ወግ እንጀምር። ታላቁ የመንግሥት ሠራተኛ ነበር። ከደመወዙ ሌላ
የሚያገኘው አበልና ጥቅማጥቅም ብቻ ሁለተኛ ቤተሰብ ሊያስተዳድር ይችል ነበር ተብሎ ይታማል። ግን
ምን ያደርጋል “አብሮ መብላቱና መጠጣት ባልነበር፤ የእንቶኔ ገንዘብ ፎቅ ይሠራ ነበር” ክሚለው የአዝማሪ
ግጥም አልዘለለም። እሱ ግን ከዚያም ያለፈ ቅሬታ ነበረውና አጋጣሚውን ተጠቅሞ ወደአሜሪካ እብስ
ይላል። በገንዘብ ረገድ ከተስፋይቱ ምድር ይልቅ አገር ቤት የተሻለ ጡንቻ
እንደነበረው ለመገንዘብ ግን ጊዜ አልወሰደበትም። እናም ከአለፍ አገደም መቶና ሁለት መቶ ዶላር ለእናቱ
ከመወርወር ያለፈ ምንም ሊያደርግ አልቻለም። አንድ አሥርት ዓመት እንዲያ ነጎደ።
ታናሹ የሠፈሩ ልጅ ደግሞ ዲቪ እሚባለው ዕጣ ወጥቶለት ወይም ወጥቶበት በዘመነኛው ቦይንግ
አቆራርጦ ዋሽንግተን ዲ ሲ ዱብ ይላል። እንደዚያኛው ወረቀቱን እስኪያገኝ እንኳ መቅለስለስ ሳያስፈልገው
ሥራ ያገኛል። ለእናቱና አባቱ ለእህቶቹና ወንድሞቹ ብቻ አይደለም ዶላር መበጠስ የጀመረው። አብሮ
አደጎቹን የቅርብ ጓደኞቹን ጎረቤቶቹንና ሌሎችንም የአሜሪካን ብር ረጨባቸው። ይባስ ብሎ በሁለተኛ
ዓመቱ ለጉብኝት ወደሸገር ተሻገረና ታላላቅ ጀብዶችን ፈጸመ። የመጀመሪያው ለእናቱ የተንጣለለ ቪላ
መግዛቱ ነው። መጀመሪያውንም የሠፈሩ ጭቃ አንገፍግፎአቸው የነበሩት እኒያ እናት አቧራውንም
ተሰናብተው ወደዘመናዊ መንደር ዘለቁ። ድኅነትንማ ባለፉት ሁለት ዓመታት በዶላር መዶሻ አናቱን
መምታት ችለዋል። ታናሽ እህቱ የራሷን የጸጉር ቤት ሥራ እንድትጀምር ወንድሙ ደግሞ የግሉን ታክሲ
እንዲያሽከረክር ለማድረግ ሁለት ሣምንት አልፈጀበትም። ሰላምታ ሊሰጡ የመጡ ሁሉ እጃቸው
የተጨበጠው በድፍን መቶ ብር ነበርና የመንደሩ ሰበር ዜና የእርሱ ለጉብኝት መምጣት ሆነ። እንግዲህ
ማለቅ አይቀርምና ለሁለት ዓመት የከሰባትን በትኖ ለሌላ ሽቀላ በቦሌ ሲሰናበት የመንደሩ ወሬ ተቀየረ።
ተረስቶ የነበረውና አሜሪካ ከገባ 10 ዓመት ያስቆጠረው የእትዬ እከሊት ልጅ ነገር ተነሳ። የቡና ማጣጫም
ሆነ። እናቱ እሁንም በቀበሌ ቤት ነው የሚኖሩት። ጉብኝት እምትባል አስቦ አያውቅም። እናም ስሙ በክፉ
ተነሳ። ከዚያ ሳተና
መቶ መቶ ብር የተቀበሉትና ለእናቱም ቤት ምርቃት ግብር የበሉት የመንደሩ ሰዎች ይህኛውን ረገሙት።
ራስ ወዳድ፤ ሆዳም፤ ሕሊና ቢስ አሉት። ለመሆኑ የነዚህ ሁለት መንደርተኞች ታሪክ ለየቅል የመሆኑ
ምሥጢር ምንድነው? አዎን ምሥጢሩ የሚሠሩት ሥራ ነው። ታላቁ ይሠራል። የሚበቃውን ያገኛል።
ታናሹ ግን የሚያበላ ሥራ ነው እሚሠራው። እሚያበላ ሥራስ ምንድነው? እሚያበላ ሥራማ ደሞዝ
መጠበቅ ሳያስፈልግ ዶላር እንደቡና ቁርስ እሚዘገንበት ነው። የሳምንቱ ክፍያ በአንድ ቀን ውስጥ
እሚመነተፍበት ነው። አስረጂዎች እነሆ!
በቅርቡ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ቀዳሚ መወያያ ከሆኑት መሃል ፍርድ ቤት የቀረቡት ሁለት የኛ ሰዎች
ናቸው። እናም ገና በተጀመረው አዲሱ የአውሮፓውያን ዓመት መባቻ ስማችንን አስጠርተዋል። በመኪናዬ
ሬዲዮ መሠረት የሚል ስም ሲጠራ ልማደኛዋ መሢ ቦስተን መጥታ ያሸነፈች መስሎኝ ነበር። ለካስ
ጨዋታው የእንብላው ሩጫ ኖሮአል። በቀጥታ ወደጉዳዩ እንዝለቅ።
ነዋሪነቱን በሲልቨር ስፕሪንግ ያደረገው የ37 ዓመቱ መሠረት ተረፈ በአሌክሳንደሪያ ፌዴራል ፍርድ ቤት
ቀርቦ የአንድ ዓመት ከስምንት ወር እስራት የተፈረደበት ሲሆን ሳያስፈቅድ የወሰደውንም $487,000
እንዲመልስ ተነግሮታል። በሰሜን ቨርጂኒያ ብሔራዊ የአየርና ሕዋው ሙዚየም በሠራባቸው ሦስት
ዓመታት ማታ ማታ ብሩን በእጅ ሻንጣ እያጨቀ ወደመኪናው የኋላ ኮፈን ይከት የነበረው ተሬ
$218,000 ያህሉ በአፓርትመንቱ ውስጥ እንደቆለፈበት ተገኝቶአል። ቀሪውን ገንዘብ አ/አ ውስጥ
ኮንዶሚኒየም እንደገዛበት ታውቋል።
በቀን እስከ $4,000 በመመንተፍ ካስተናገደቻቸው 59,712 የሚገመቱ መኪኖች የተገኘውን ገቢ አንድ
ሦስተኛውን ለራሷ አስቀርታለች የተባለችው የ46 ዓመቷ ፍሬወይኒ መብራህቱ ደግሞ $900,000 ዶላር
መስረቋን አምናለች።. የ27 ወራት እስራት ነው የተፈረደባት.ሲሆን ስትለቀቅም ለሌላ ሦስት ዓመታት
በዐይነ ቁራኛ እንድትጠበቅ ተብሎአል። በተጨማሪም $895,680 እንድትከፍል ታዛለች።
“ገንዘቡን ለልጆቿ የኮሌጅ ክፍያ ለሴት ልጅዋ የቀዶ ሕክምና ወጪ አውላዋለች። ወደአገር ቤት
መድኃኒትና ልብሶችን ልካበታለች። ለመስጊዶችም ስጦታ አበርክታለች” ይላል የፌዴራሉ ምርመራ
ቢሮ(ኤፍ.ቢ.አይ)ዘገባ። አርቆ አሳቢዋ ፍሬወይኒ በራሷ ብቻ አልተወሰነችም። ሌሎች ባልደረቦቿንም
እንዴት መመንተፍ እንደሚቻል አስተምራቸዋለች። እነርሱ በቅንነት ከሠሩ የገንዘቡ ልዩነት ሊታስነቃ
ይችላልና።
ለመሆኑ እንዴት ተደረሰባቸው? በጥቆማ ነው። ከዚያም ከሙዚየሙና ከኤፍ.ቢ.አይ የተውጣጡ
ባለሙያዎች ወጪ ገቢዎቹን መኪኖች እየቆጠሩ ከማታው ሪፖርት ጋር ማመሳከር ጀመሩ።
የሙዚየሞቹ ቃል አቀባይ የሆኑት ክሌይር ብራውን በበኩላቸው “የሚያቀርቡት ዘገባና ገቢው ተመሳሳይ
በመሆኑ ዝርፊያ ይኖራል የሚል ጥርጣሬ አልነበረንም” ይላሉ። ባለፉት ሦስት ዓመታት ጋራዡ ሊያገኝ
ከሚገባው ገንዘብ አስር ከመቶው ሁለቱ ወገኖቻችን ኪስ ወድቋል እንደዐዋቂዎቹ ስሌት። ምን ያህል
መኪኖች እንደገቡ የሚያሳየውን ማሽን በመንቀልና የየቀኑንም ዘገባ በመሸቀብ ከ2009 ጀምሮ $1.4
ሚሊዮን ዶላር ከድርጅቱ ተዘርፎአል።.
ሌላዋና ሦስተኛዋ ተጠርጣሪ $120,000 ወስዳለች በሚል ጉዳይዋ በፍርድ ቤት ሊታይ ቢቀጠርም
ቀድማ ራሷን በመግደልዋ ፋይሉ ተዘግቷል። የፍርድ ቤቱ ሪፖርት ስሟን ያላነሳ ቢሆንም ናዝሬት በተሰኘ
ድረ ገጽ ላይ ስሟ ገነት እንደሚባል አንብቤያለሁ። እንግዲህ እስዋም የኛው ሰው ነበረች ማለት ነው።
እኒህ ሦስት ግለሰቦች እንግዲህ የድርጅቱን ቴክኖሎጂ ለማሳደግ አስተዋፅዖ አድርገዋል ካልተባለ በቀር
በምንም መንገድ የሚመሰገኑበት ቀዳዳ የለም። ግን ድርጅቱ እዲስ ዓይነት የቁጥጥር ማሽን ዘርግቶአልና
በዚያ ሊታወሱ ይችላሉ። ለማንኛውም እንዲያ እንዲያ እያሉ የአገራችን ቁጭበሉዎች የአሜሪካን ኢኮኖሚ
ብቻ ሳይሆን የማኅበረሰባችንንም ስም እየቦጠቦጡ ነው።
አንድ ተማሪ ወደኮሌጅ ሊገባ ያመለክትና ርዕሦችን መርጦ ጽሑፍ እንዲያቀርብ ይጠየቃል። እናም
ስለእግዚአብሔር እና ስለሰይጣን የሚያውቀውን አንድ አንድ ገጽ እንዲጽፍ ይነገረውና ይጀምራል።
በተለይ ስለእግዚአብሔር መልካምነት የሚችለውን ሁሉ ባማሩ ቃላት ሲከሽን ይቆይና ሰዓቱ ያልቅበታል።
ይህን ጊዜ ስለሰይጣን እንዲጽፍ በተሰጠው ሥፍራ ላይ አንዲት ዐረፍተ ነገር በጥድፊያ ጭሮ መለሰ አሉ።፡
”ስለሰይጣን ለመጻፍ ጊዜ የለኝም!”
እኔም ይህችን የጫርኩት በተመሳሳይ ስሜት ውስጥ ሆኜ ነው። ከእኛው መሃል በበጎ ምግባርም ይሁን
በልቀት የሚመሰገኑ ሲኖሩ ስለነርሱ ብጽፍ ደስ ይለኛል። ስለሌቦች ለመጻፍ ግን ከዚህ በላይ ጊዜ የለኝም።

Sunday, May 19, 2013

የማዕበል መንገደኞች


የማዕበል መንገደኞች

የዚህች መጽሓፍ ዓላማ ውኃው በመርከቦችና በውስጡም ባሉ ሰዎች ላይ የሚያደርሰውን እንግልት መተረክ አይደለም። ይልቁንም እንደ ማዕበል ስለሚያንገላታን ምድራዊ ኑሮ ግንዛቤ ማስጨበጥ ነው። ከምንም ይልቅ የዚህች ጥራዝ ተልዕኮ የማዕበል መንገደኞች መሆናችንን ማስታወስ ነው።

ውስጣዊው ነውጥ ማንነትን ይሞግታል። ሰው ሠራሽና ተፈጥሮአዊ አደጋዎችም ቢሆኑ አናዋጮች ናቸው። ልክ ማዕበሉ መርከቦችን እንደሚያንገላታቸው ከግራ ወደ ቀኝም እንደሚያላትማቸው እንዲሁ የሰውን ልጅ ያደርጉታል። ይንጡታል። ያፈናቅሉታል። አንዳንዶቹን እንጂ ሁሉንም ማስወገድ ደግሞ አንችልም። ናዳውን በእርከን መገደቡ ተሳክቶልናል። ዐውሎ ነፋሱን ግን ለመከልከል የሚያስችል ቴክኖሎጂ አላገኘንም። እናም ነውጡ አብሮን ይኖራል።  ለዚህ ነው የማዕበል መንገደኞች መባላችን።
                         
ከውስጥ ገጾች

Sunday, March 10, 2013

መቋጫ

መቋጫ
ነገሩ ባልከፋ
ዶሮች አርብተሃል፣
ዕንቁላል መሰብሰብ
እንዴት ይሣንሃል?
ምንጭ- ለተሰጠኝ ዕድሜ
ገጣሚ ዓለማየሁ ማሞ