Tuesday, December 22, 2015

ታላቁ ሩጫ!


ሩጫችንን እንጨርስ!
(ቁልፍ አሳቦች በዓለማየሁ ማሞ)
ሰው ሁሉ ይሮጣል። ወደ የትና ለምን ይሮጣል ከተባለ እርሱ ሌላ አነጋጋሪ ጥያቄ ነው።
ከሽልማቱ ውድድሩ ከውድድሩም ልምምዱ ይቀድማል።
ሮጣለሁ የሚል ሰው ሊያደርጋቸው ከሚገቡ ወሳኝ ነገሮች አንዱ ሸክሙን ማራገፍ ነው።
ሕጉን አናክብር። ሯጭነታችን ከሕግ ማምለጫ አገልግሎታችንም ከሥርዓት ማፈንገጫ አይሆነንም።
የክብሩን ውድድር በብቃት ለመጨረስና ለመሸለም የሕጉ እውቀት ያስፈልጋል።
የወደቀውን የሚያነሡ የተፍገመገመውን የሚያበረቱ ቅን ሰዎች በብዛት የሚፈለጉት በሩጫው ሜዳ ላይ ነው።
ሰማያዊው ሩጫ ሲታሰብ በክርስቶስ የመስቀል ሥራ የምናምን ሁሉ የአንድ ቡድን ተሰላፊዎች ነን።
ከአቅማችን በላይ መሮጥ መጀመሪያ ድካምን ቀጥሎም ዝለትን ያመጣብናል። ያኔ ማቋረጥ የሚባል ክፉ አማራጭ ከፊታችን ይደቀናል።
አማራጩ ወደ ኋላ መመለስ አቋራጩ ማመቻመች አይደለም። መጽናት ነው።
ሩጫውን ጨርሻለሁ ለማለት መጀመሪያ ሳያቋርጡ መሮጥ ያሻል።
ምድራዊው ሽልማት አላፊና ጠፊ ነው። እኛ ግን ለማይጠፋው ሽልማት እንሮጣለን።
የዛሬ ሯጮች እኛ ነን። የምሕረት ደጅ ሳይዘጋ ክፉዎቹ ቀኖችም ሳይመጡ ወደ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም እንሩጥ። እንጨርስ:: ከመነሻችን ይልቅ መድረሻችን ይቀርባል፤ ከመመለስም ይልቅ መጨረሱ ይቀለናል!
ታላቁ ሩጫ ከሚለው መጽሓፌ 

Saturday, September 5, 2015

ሩጫው መከራ አለበት

ከሦስት ሳምንታት በፊት በጆርጅያ አንድ የሕዝብ ት/ቤት ውስጥ የተካሄደው የጥምቀት ሥርዓትና “እግዚአብሔር አሁንም በትምህርት ቤቶቻችን ውስጥ በሥራ ላይ ነው” በሚል መሪ ዐረፍተ ነገር ዩቱብ ላይ የተለቀቀው ይህንኑ የሚያሳይ  ቪዲዮ ውዝግብ አስነሥቷል። ቪዲዮው የተከላካዮች አሠልጣኝና የስፖርት መምህሩን ጨምሮ 18 የቪላ ሪካ እግር ኳስ ቡድን ተጫዋቾች በየተራ ሲጠመቁ ያሳያል።
ነፃነት ከኃይማኖት(Freedom from Religion) የተሰኘ ድርጅት ፕሬዚዳንት የሆኑት ሎሪ ጌይለር "ልጆቻችን እንድትጫወቱ ጸልዩ ተብለው ሊገደዱ አይገባም።  ይህ ማስፈራራትና  እምነትን ማስካድ ነው" ሲሉ ድርጊቱን ተቃውመዋል። ለት/ ቤቱ   በጻፉት ደብዳቤም "አስቸኳይ ምርመራ አድርጎ እርምጃ እንዲወስድና ከዚህም በኋላ ይህ ዓይነቱ ሕገወጥ ሃይማኖታዊ ልምምድ እንዲቆም እንጠይቃለን” ሲሉ አሳስበዋል”። በነገራችን ላይ ይህ ድርጅት ቀደም ብሎም እዚያው ጆርጂያ ያለ ሌላ ት/ ቤትን ከሦ እንደነበር ይታወሳል። “ይጸልያሉ” ብሎ!
በኬንታኪ ደግሞ ግብረሰዶማዊ ጋብቻ የመጀመሪያውን ሠርቲፊኬት የተቀበሉት ዊልያም ስሚዝና ጄምስ ዬትስ ገና ፈንድቀው አላባሩም። ስድስት ዓመታት ሙሉ የደከሙለት ዐመፅ ጊዜያዊ ድል አግኝቶአልና።ተጋቢዎቹ ገና ፍርድ ቤቱ ከመከፈቱ በሁለት ሰዓት እዚያ የተገኘኡ ሲሆን ደጋፊዎቻቸውም “ፍቅር ያሸንፋል” እያሉ ይጮኹ ነበር። ድንቄም!
ይህንን አልፈቅድም ብላ የተቃወመችው ኪም ዴቪስ የት ናት? እሥር ቤት!
ምን በደለች?
የአዳምና ሔዋንን እንጂ የአዳምና ብሩስን ጋብቻ አልቀበልም ብላ!
የእምነት ነፃነት ተምሳሌት በምትባለው አሜሪካም ጭምር አንድ እውነት እየበራልን ነው። በርግጥ ክርስቶስን እየመሰሉ ለመኖር የሚወድዱ ይሰደዳሉ። ያፈጠጠና የተረሳ እውነት ይኸው! ሰማያዊው ሩጫ መከራ አለበት። አዎን ጭብጨባና ፉጨት ላያጅበን ይችላል። እንዲያውም ተቃውሞና ስደት ሊያባርረን መቻሉ ግልጽ ነው። በየመንገዱ የሚቀመስ ውኃ በማቀበል ፈንታ ገዝተን የጨበጥነውን እንኳ ከእጃችን የሚያራግፉ የዲያብሎስ ጎረምሳ ልጆች ያገኙን ይሆናል። ከፊትና ኋላችን የሚንጋጋው ተሽከርካሪ የመጀመሪያ እርዳታ ሰጭ መሆኑ ቀርቶ ሊገጨን የተላከ የሞት መልእክተኛ ሊሆንም ይችላል። እናም ሰማያዊው ሩጫ ከምድራዊው በመከራ ይለያል።የቀደሙት ቅዱሳንም ሩጫቸውን የጨረሱት በብዙ አበሳ ነው። ከቤተሰባቸው ጀምሮ አሳዳጃቸው ብዙ ነበር። መንግሥታት መከራቸውን አብልተዋቸዋል። ከአንበሳ ጋር እንዲታገሉ በተራበ አውሬ እንዲበሉ አድርገዋቸዋል።
የዕብራውያን ጸሓፊ ይህንኑ ሲያስረግጥ እንዲህ ይለናል። “ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፥ የእሳትን ኃይል አጠፉ፥ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፥ ከድካማቸው በረቱ፥ በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ፥ የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ። ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤ ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤ በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ተፈተኑ፥ በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ (ዕብ. 12፡ 34-38)።
አልሰማሁም እንዳትል.....አልሰማሁም እንዳትይ....
በተመሳሳይ አሳብ ላይ ለመናገር ከቤቴ ከመውጣቴ በፊት ....

Thursday, August 20, 2015

ተከስተ ዳግም ተከሠተ!


እዚሁ ሲልቨር ስፕሪንግ “አንድ ልብ” በሚል መሪ አሳብ በቅርቡ የተካሄደ   ኮንፍራንስ ነበር። በነሐሴ 8 2015 ቅዳሜ ቀን  ለወራት ያልታየው ዘማሪ ድምፅ ማጉያውን ጨበጠ። ታዳሚዎቹም ተነሥተው በጭብጨባ ተቀበሉት።
እንግዲህ በሰሜን አሜሪካና አካባቢው የሰሞኑ ዐበይት ወሬ “ተከስተ ዳግም ተከሰተ” የሚል ሊሆን ነው። መቼም ወሬ ከነሁሴን ቦልት ፈጥኖ ይሮጣልና ደግሞ ዓለምን ሊያደርስ ነው። ያንን ተከትሎ ደግሞ ዝርወተ ኢትዮጵያውያኑ እንደ ጨው በተበተኑበት ሁሉ “መቼ፣ እንዴት፣ ለምን፣ የት እና ወዴት” የተሰኙ ማብቂያ የለሽ ጥያቄዎች በዘማሪው ዳራና መፃዒ ዘመን ዙሪያ በማኪያቶ ሊወራረዱ ነው።
አስቀድሞ ያንን ጥም ለመቁረጥ ይህችን አጭር መረጃ መልቀቁ ሙያዊና ወንድማዊ ግዴታዬ ሆኖ አገኘሁት።  ዝርዝሩን እንደወረደ...
መረጃው እንደደረሰኝ ፓስተር ተከስተ ጌትነት ወደሚያገለግልባት የፀጋ ቤተ ክርስቲያን ስልክ መታሁ። መጋቢ መስፍን አስፋውን አግኝቼ ስላለፉት 12 ወራት ዋና ያለውን እንዲነግረኝ ጋበዝኩት። በየሳምንቱ እየተገናኙ ሲጸልዩና ሲመካከሩ እንደነበር በግልጽ አስረዳኝ። አሁን ወደ መድረክ ስለመመለሱ የምሰማው ወሬ እውነት ነው እንዴ አልኩና ለመስማት ተዘጋጀሁ። አንደበተ ርትዑ ወዳጄ ለመልሱ አላመነታም። “አዎ” አለኝ “አዎ፤ በሦስት ዓይነተኛ ምክንያቶች ወደ አገልግሎቱ ልንመልሰው ነው። በመጀመሪያ በውድቀቱ ተፀፅቷል። በሁለተኛ ደረጃ የጣልንበትን የአንድ ዓመት እገዳ ያለምንም ማንገራገር ጨርሷል። በመጨረሻም በነዚህ ወራት ከእኛ ሳይለይ የአባልነት ግዴታውን ተወጥቷል። ስለተደረገለት ክትትልና ስለተቀበለው የተሐድሦ ትምህርት ማወቅ ከፈለግህ ግን በዚህ የረዱንን ፊላደልፊያና ሳንፍራንሲስኮ ያሉ ሁለት መጋቢዎች ማግኘት ይኖርብሃል።”
በማግሥቱ ደግሞ ስልኬን ወደ ካሊፎርኒያ አዙሬ ፓስተር ተስፋዬ ተሰማን አገኘሁት። በርግጥም ይህ ጥያቄ ቀርቦለት ነበር። “በመካከላችን ያለውን ርቀት በማጤን ይልቁንም በሁለቱ መካከል ለረጅም ጊዜያት የተገነባውን የአማካሪና መካሪ ዝምድና በማጤን ፓስተር እንዳልክ ጉዳዩን እንዲይዘው ሁላችን ተስማማን ” ብሎኛል።  ይህ ውይይት የሦስት ሰዓት መንገድ ወደሚርቀን ፓስተር እንዳልካቸው ሣሕሌ መለሰኝ። የአራት ኪሎው ወዳጄ ደግሞ ሁለቴ ያቃጨለውን ስልክ አንሥቶ መለሰልኝ።
እሱም በበኩሉ ጥያቄዬን በጥሞና ካደመጠ በኋላ  “አዎን የረጅም ጊዜ ትውውቃችን፣ በበዓለ ሲመቱ ላይ መገኘቴና ይልቁንም ቤተ ክርስቲያናቸው ከጣለችብኝ አደራ የተነሣ ብዙ ጊዜ አብሬው አሳልፌአለሁ። ዝርዝሩን ግን ለነርሱ ካቀረብኩት ሪፖርት ማግኘቱ ይቀልሃል”አለና ስልኩን ሳንዘጋው በፊት ደብዳቤውን ከፊላደልፊያ ኢሜል አደረገልኝ።
ወዲያውኑ ከፍቼ አነበብኩት።
በፊላደልፊያ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤ/ክ ዋና መጋቢና የኮምፓስ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር የሆነው እንዳልካቸው የላከው ደብዳቤ ይዘትም መስፍን ከነገረኝ ጋር የሚታረቅ ነው። ስለዚህ ዋና ዋና ቁም ነገሮቹን እንደሚከተለው ጨምቄአቸዋለሁ።
ከጥቅምት ወር 2014 ጀምሮ በራስ ተነሣሽነት ሲመክረውና  ሲጸልይለትም ቆይቷል። የካቲት 15 2015 ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱ በይፋ ደብዳቤ የፓስተሩን ርዳታ ጠይቃለች። ይህኔ ደግሞ ባለቤቲቱንም  በመጨመር በርካታ ጊዜያት እያገኛቸው አደራውን ለመወጣት ይተጋል። ተሳክቶለትማል።
እንደ ደብዳቤው ከሆነ 38 ሰዓቶችን ለተሐድሦ ትምህርት ምክርና ጸሎት የተጠቀሙ ሲሆን ዘጠኝ ለሚያህሉ ሰዓቶች ደግሞ እንዳልክና ተከስተ የምሥራችን (የተከስተ ባለቤት) ጨምረው ተመካክረዋል። አንድ ጊዜ ባለጉዳዩ ወደ ፔንሲልቬኒያ ከመሄዱ በስተቀር ቀሪውን ጊዜ ባለአደራው ወደ ሜሪላንድ መመላለሰ እንደነበረበትም ደብዳቤው አብራርቷል። በነዚህ ጊዜያት ያተኮሩባቸውን አራት ዋና ጉዳዮች አማካሪው ዘርዝሮ የጻፋቸው ሲሆን ፍሬ ነገራቸው ይህንን ይመስላል።
 ሀ) ጥፋትን ማመን፣ መናዘዝና የእግዚአብሔርን ይቅርታ ማግኘት ለ) ውድቀቱን ላለመድገም በመከላከል ላይ ያተኮረ ትምህርት  ሐ)በመሃሉ ቅድሚያ በመስጠት የተጎዳውን ትዳር መጠገን፣ በታቀዱ የግል ጊዜዎች በመታገዝ ፍቅርን ማሳደግ መ) ከአገልግሎቱ ዘዋሪነትና ተፈላጊነት አንጻር ሊወሰድ የሚገባው ጥንቃቄ የሚሉ ናቸው።
ፓስተር እንዳልካቸው ከሰደደው ከዚሁ ሁለት ገጽ ደብዳቤ ውስጥ የግል አስተያየቱንም ጨምሯል። በዚሁም መሠረት የንስሐ ቆይታውን በአጥጋቢ ሁኔታ እንደፈጸመ ይልቁንም የተሰጠውን አገልግሎት(ትምህርት፣ ምክርና ጸሎት) በብዙ ትኅትናና ፈቃደኝነት ተከታትሎ እንደጨረሰ ካወሳ በኋላ  “ቤተ ክርስቲያኒቱ ምስክርነቴን ተቀብላ ...ቀሪ እርምጃዎች ካሉ በማስፈጸም ...አገልግሎቱን የሚጀምርበትን ሁኔታ እንደምታመቻች እምነቴን እገልጣለሁ”  በማለት ይህ ምኞቱና ጸሎቱ እንደሆነም አበክሮ በመግለጽ ደምድሟል።
ቤተ ክርስቲያኗ በበኩሏ በዚሁ የተስማማች ቀሪ ሥራዋንም ያጠናቀቀች መሆኑ እየታየ ነው። ከላይ የጠቀስኩት የመጋቢው እማኝነት እንዳለ ሆኖ  በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ነሐሴ 29 ይህንኑ የሚያውጅ ስብሰባ አዘጋጅታለች። ያኔ ቦስተን ስለምሆን ለእናንተ አንባቢዎቼ የዐይን ምስክርነት አይኖረኝም። እናም ሰበር  ዜና ይዤላችሁ መጣሁ።   
እንግዲህ ተኬ ዳግም ሊከሰት ነው። በዓመታት መካከል በአገልግሎቱ ብዙ ተጠቅመናል። በዝማሬዎቹም ተባርከናል። አሁን ሲመለስ የመጀመሪያ ዜማው ምን ይል ይሆን?  እንደኔ ግምት “ጠላቴ ሆይ ደስ አይበልህ፤ ብወድቅ እንኳን እነሣለሁ” ሳይሆን አይቀርም።
በነገራችን ላይ ተከስተን እወደዋለሁ!


Saturday, March 21, 2015

"መመለሻዬ ደረሰ!"

ማን ብለን እናስታውስህ?
ዓለማየሁ ማሞ የሚለው ስሜ አሁንም አልተቀየረም። ደራሲና ጋዜጠኛ ነኝ። ያ ካልበቃም ገጣሚና ተርጓሚ የሚለውን ማከል ይቻላል። አሜሪካ በሚሉት አገር ሜሪላንድ ክፍለ ግዛት አስፐን ሒል ከተሰኘች ከተማ እኖራለሁ።
የአንተ መጻሕፍት በመደርደሪያዎች ላይ ከታዩ ዓመታት ተቆጠሩ። መጻፍ አቆምክ እንዴ?
ልክ ነው። አስራ አምስት ዓመታት ነጎዱ። ምክንያቱ ከትውልድ አገሬ 10000 ማይሎች ርቄ መኖሬ ነው። መጻፍ እንኳ ጨመርኩ እንጂ አላቆምኩም። ግን መጻሕፍቱን አዲስ አበባ ላይ ለማሳተም ሁነኛ ሰው አልነበረኝም። ሁነኛ ያልኩት ሰው የገንዘብ አያያዙ ጠፍቶበት ዐይቼ ተሳቀቅሁና ለዓመታት ሸሸሁ። በዚያ ላይ አስባታሊው የኑሮ ዘይቤ ፋታ አልሰጠኝም። ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት መሆኔ፤ እስከ አርባ ሰዓቶች በሳምንት መሥራቴና ትምህርት ቤት መሄዴ በቀን ጥቂት ሰዓቶች የሚበቁት አይደለም። ይሄ ሁሉ አንሦ አሁንም መጻፌ ራሱ እንደተአምር መቆጠር አለበት።
በርግጥም ርቀህ ቆይተሃል። እና የጻፍካቸው በሙሉ ለመታተም ጊዜ እየጠበቁ ነው ማለት ነው?
ለነገሩ ጥቂት ጥቂት እያደረግሁ ሚሽጋን ላይ አሳትሜአቸዋለሁ። ግን ያገኟቸው በሰሜን አሜሪካ ውሱን ክፍለ ግዛቶች የሚኖሩና አውሮፓ ያሉ አንባብያን ናቸው።  የላክሁላቸውና በ2011 ለጉብኝት የመጣሁ ጊዜ እጃቸው ላይ ያኖርኩላቸው ጥቂት የአዲስ አበባ ወዳጆቼ ብቻ መጻሕፍቱን ነክተዋቸዋል። ነጋ ጠባ የመረቀኝ አንባቢ ግን አላያቸውም።
በውሱን ክፍለ ግዛቶች አልክ? በሠለጠነው ዓለም መላውን አሜሪካ እንኳን  ማዳረስ አልቻልክም?
አዎን ከአምሳዎቹ ክፍለ ግዛቶች ውስጥ ሃያውን ብቻ ነው በብዙም ይሁን በጥቂቱ የነካኋቸው። ለምን ወደሚለው ከገባን በመጀመሪያ በሁሉም ክፍለ ግዛቶች ውስጥ አበሻ አለ ማለት አይቻልም። በዚያ ላይ ሰዶ ማሳደድ አልወድም። አገሬን ለቅቄ የሄድኩበትን ምክንያቶች ሳስብ አንዱና ትልቁ እርሱ ነው። አዎን አንዱ የመጻሕፍት ገንዘብ ስብሰባ ያመጣብኝ መከራ ነው። በተለይ ባለመዝሙር ቤቶች ነን ይሉ የነበሩትን ጥቂት ቁጭ በሉዎች መታገሥ አልሆነልኝም። ቁጭ ብዬ ልጻፍ ወይስ እነርሱ ዘንድ ልመላለስ? የእምነትና የመጻፍ መብት በተከበረባት አገር መኖሬ የቆመው በዚህና ሌሎች ምክንያቶች መሆኑን ሳስብ አሁንም እቆዝማለሁ። ወደ”ተስፋይቱ ምድር” ከመጣሁም በኋላ እነዚያው ሰዎች ቀድመውኝ ውቅያኖስ አቋርጠውና ተደላድለው አገኘኋቸው። ግን ምን አማራጭ ነበረኝ? ከዚህ ወዴት ልሂድ? በቆይታዬ አሜሪካ የገቡ እንጂ አሜሪካ ያልገባቻቸው ጥቂት እንዳይደሉ ተረድቻለሁ። ከዚህን የተነሣ ጥቂት የማይባሉና መንፈሱ የላላ ሰው ካገኙ ለሕመም የሚዳርጉ ገጠመኞች አሉኝ።
ከነዚያ ዋና የምትላቸው የትኞቹን ነው?
 እንግዲያው ሦስት ቦታዎች ላይ የገጠመኝን ላውሳ። በ2005 ዓ.ም  ሦስቱን ኩታ ገጠም ክፍለ ግዛቶች ማለትም ሜሪላንድ፤ ዲሲና ቨርጂኒያን ያማክላሉ ባልኳቸው ሦስት መደብሮች በወቅቱ ያሳተምኩትን መጽሐፍ ለሽያጭ አስቀምጬ ነበር። በነገራችን ላይ ውሉ በሚሸጡት መጻሕፍት ልክ ለእነርሱ ድርሻቸውን ማካፈልን ይጨምራል። ስለዚህ ተጨማሪ ንግድ እንጂ በጎ አድራጎት አይደለም። በዚያው ሰሞን ከመስታወት ሬዲዮ አዘጋጅ ጋር ቃለ ምልልስ አድርጌ ነበር። በዚያም ግለት ታግዞ መጽሐፉ ፈጥኖ ተሸጠና አለቀ። ገንዘቡን ለመሰብሰብ ስሞክር ግን  ፈገግ የሚያሰኙና የሚያስቆዝሙ ነገሮች አጋጠሙኝ።
መጀመሪያ የሄድኩት ዘጠነኛውና ዩ መንገዶች መጋጠሚያ ላይ ነበር። “ባለቤቱ የለም” ብለው አሰናበቱኝ። ይህኔ እኒያ ባለመዝሙር ቤቶች ትዝ አሉኝ። ከላይ እንዳልኩት ከአገሬ ለመውጣት ውሳኔ ላይ ካደረሱኝ በርካታ ምክንያቶች የአንዱ ፈጣሪ የሆኑት ቁጭበሉዎች  ሲቀበሉ የሚያሳዩት ፈገግታ ብር አምጡ ሲባሉ ይጨልም ነበር።
ሁለተኛው ደግሞ ስንት መጽሐፍ እንዳስቀመጥኩ እኔኑ መልሶ ጠየቀኝ። አሜሪካ የሚኖር ነጋዴ የተረከበውን ቁራጭ ወረቀት ላይ አለመጻፉ ቢያሳዝነኝም ሃያ መሆኑን ነገርኩት። “ወዳጄ እኛ ከደራሲያን የምንቀበለው አምስት መጽሐፍ ብቻ ነው። በጣም ከበዛ አስር። ለምን ቢባል የኛ ሰው አያነብም። በል የአስር መጽሐፍ ዋጋ በቼክ ጽፌ አስቀምጥልሃለሁ” አለና መልሴን ሳይሰማ ስልኩን ዘጋ። ሰማንያ በመቶውን ለራሱ አስቀረ ማለት ነው።
ከሁሉ አስገራሚው ሜሪላንድ የገጠመኝ ነው። ወደ መደብሩ ስሄድ አንዲት እናት ተቀምጠዋል። እንዲህ ዓይነት ዕድሜ ላይ ያሉ እናቶች ብዙ ጊዜ ሞግዚቶች ናቸው እንጂ መደብር ውስጥ አይቀመጡም። ከተቀመጡበት የማይነቃነቁት ሴትዮ ታዲያ ዋጋ ስለማያውቁ አንድ ነገር ሲጠየቁ ስልክ ይመቱና ከባለቤቲቱ ይጠይቃሉ። በወጣትነታችው አራዳ እንደነበሩ ለመገመት ሞከርኩና ተውኩት። ግን ሰላምታ አቅርቤ ትንሽ ካዋራኋቸው በኋላ ስለራሴ መጽሐፍ እንደገዢ ጥያቄ አቀረብኩ። አለመኖሩን ነገሩኝ። በጣም እንደምፈልገው አሳስቤ ስጠይቃቸው ምን እንዳሉኝ ታውቃለህ? “ደራሲው ፈላጊ እንደሌልው ስላወቀ ሰብስቦ ወስዶታል!”። ደራሲው እኔ መሆኑን ገልጬ ባፋጥጣቸውም መልሰው ልቤን አደረቁኝ እንጂ አሮጊቷ አልደነገጡም።
እነዚህን ገጠመኞች ዘጠኝ ዓመት ሙሉ ስቄ ለመሳቂያ አድርጌአቸዋለሁ። አንዱ የመጻፍ ለዛ የደረሱብንን ክፉ ነገሮች ስንቀልድባችው የሚንጠፈጠፈው ወዘና ነው። በጥቅሉ ግን ጥቂት የማይባሉ ሰዎች እዚህ ሲመጡ ከመሻሻል ይልቅ ብሶባቸዋል። የሰዓትን አከባበርን ነገርማ እንተወው።
አንስተኸዋልና ባንተወው። ይልቅ ስለሰዓት አከባበር ምን ታዘብክ?
አንድ የፌስቡክ ወዳጄ ለጥፎት ዐይቼ ባሳቀኝ አባባል ልጀምር። ስለእኛ ቀጠሮ ነው። “ከ5-6 እመጣለሁ፤ ከ7-8 ዐይተኸኝ ካልመጣሁ ከ9-10 ሂድ” ይላል። ከመጋነኑ በስተቀር ውሸት ነው ብሎ የሚከራከር የለም። መጽሓፍ በኪሴ ይዤ “ባለቀጠሮዎች” እስኪመጡ መጠበቅ ዕድል ፈንታዬ ነበር። ከቀኑ ሰባት ሰዓት የሚጀምር አንድ ስብሰባ ላይ እንድናገር ተጋብዤ ዘጠኝ ተኩል ላይ ነው መድረኩ የተሰጠኝ። ወሬዬን አሳጥሬ ወደሚቀጥለው ፕሮግራም ለመሄድ ከመድረክ በቀጥታ ወደመኪናዬ ተወነጨፍኩ። እአሁን አሁን  ግን የቅርብ ወዳጆቼም ተመሳሳይ አቋም ይዘዋልና አብረን መቋቋም ጀመረናል። በሦስትዮሹ የመጻሕፍት ምረቃ ላይም የማይረሳ ሌላ ታሪክ ሠርቻለሁ።
ምን አደረግህ?
ፕሮግራም ስምንት ሰዓት ተኩል ነበር የታቀደው። ከተጋባዥ መቶ እንግዶች ከሩብ ሲል ሦስት ሰዎች መጡ።   በተባለው ሰዓት የደረሱልን ከሃያ የማያንሡ ከሠላሳ የማይበልጡ እንግዶቼ ብቻ ነበሩ። ሁሉም እንዲቀመጡ ካደረግሁ በኋላ ድምፅ ማጉያውን ጨበጥኩ። እንኳን ደህና መጣችሁ ካልኩ በሁዋላ በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ላይ አንዲህ አልኩ። “ግብዣው የእኔ ነውና አክብራችሁ ስለመጣችሁ አመሰግናለሁ፤ አሁን ፕሮግራሙን እነሆ ጀመርኩት። የእኛ ሰው ሰዓት አያከብርም እያለን በየመድረኩ ብዙ ተናግረናል፤ እኔና ወዳጆቼም ጽፈናል። የማርፈዱ ጣጣ ምክንያተ ብዙ ቢሆንም አንድ ያላስተዋልነውን ሰበብ ዛሬ ልንገራችሁና ንግግሬን ልጀምር። እንደ እናንተ ያሉ ሰዓት አክባሪዎች ቀድመው ይደርሳሉ። እንደ እኔ አይነቱ ደጋሽ ደግሞ አዳራሹ ሞላ እስኪልልለት ሻይ ቡና እንበል እያለ ያጉላላችኋል። በሚቀጥለው ጊዜ ታዲያ እናንተም አርፋጆች ትሆናላችሁ። እኔ ይህንን አልደግፍም። እነሆ ጀምሬአለሁ! ተንጠባጥበው የሚመጡት ይምጡ። ይህም ብቻ ሳይሆን ፕሮግራሙን በመርሃ ግብሩ መሠረት በሰዓቱ እዘጋዋለሁ።” አደረግሁት። አንድ የሬዲዮ አዘጋጅ ወዳጄ እንደነገረኝ በበነጋው የከተማው ወሬ ይኸው ነበር።
አሁን ምን እያሰብክ ነው?
ለመነበብ የማልፈነቅለው ድንጋይ የለም። ምን እያሰብክ ነው ስባል መልሴ የበለጠ ለመሥራት ነው። የስርጭት አድማሴን ለማስፋት ነው። ከምንም ይልቅ እንደመንፈሳዊ ሰው ሳሰላስል ወደ አገሬ የምመለስበት ጊዜ አሁን እንደሆነ ጠንክሮ ይሰማኛል።
መቼ ነው የምትመለሰው?
መመለስ የሚለውን ቃል በመደበኛ ትርጉሙ አይደለም የተጠቀምኩበት። መመላለስ የሚችል ሰው ስለመመለስ ለማሰብ መቸኮል አይገባውም። በፈለግሁ ጊዜ መምጣት እችላለሁ። እንዲያውም ፋይዳ ያለው ነገር በአገሬ ውስጥ ለመሥራት (በኢንቨስትመንት ፣ በበጎ አድራጎት ወይም ሌላ) እያወጣሁና እያወረድኩ ነው። ዛሬ ግን መመለስ ስል ስለእኔነቴ ሳይሆን ስለሥራዎቼ እያወራሁ ነው። በውጭ ቆይታዬ አስራ አንድ መጻሕፍትን አሳትሜአለሁ። ቀደም ብዬ እንዳነሣሁት  ሁሉም የተነበቡት በሰሜን አሜሪካና አውሮፓ ነው። እናም በየተራ አገር ቤት እንዲታተሙ አስባለሁ። መመለስ ይህ ነው። ሥራዎቼ ለወገኔ መድረስ አለባቸው። የእስካሁኑ ሙከራ ከምንም ቢሻልም ውቅያኖሱን ትቶ ኩሬ ውስጥ ከመቦጫረቅ የተለየ አልነበረም። አገሬ የምመለስበት ጊዜ አሁን ነው። አዎን መመለሻዬ ደርሷል!
አሁን ታዲያ እጅህ ከምን?
በያዝነው የአውሮፓውያን ዓመት ቢያንስ ሦስት መጻሕፍት እንዲታተሙና እንዲሠራጩ ፍላጎቱና ዝግጁነቱ አለ። አሳቤን ካልቀየርኩ በስተቀር ክፍል አንድ የሕይወት ታሪኬና የማዕበል መንገደኞች የሚለው መጽሓፍ ይህንን ዕድል ሳያገኙ አይቀሩም። ለጊዜው ግን አንድ መጽሐፍ ደግሜ በማሳተም ሕልሜን እውን ማድረግ ጀምሬአለሁ።
የትኛውን?
የብርታቱ ምሥጢር የተሰኘውን የስሚዝ ዊግልስዎርዝ የአገልግሎት ታሪክ ደግሜ አሳትሜዋለሁ። በስርጭት ላይ ነው!!!
ለምን እርሱን መረጥክ?  
በሁለት ምክንያቶች ነው። አስራ አምስት ዓመታትን ተሰውሬ ብቅ ስል አዲሶቹን ሥራዎቼን ይዤ ከምመጣ ይልቅ ቢያንስ በሚታወቀው መጀመሩ ያዋጣል። አዲሱ ትውልድ ማንነቴን ቢጠይቅ እንኳ ነባሮቹም አላለፉምና ዓለማየሁ ማን እንደሆነ ይነግሩታል። ሌላው ምክንያት ደግሞ ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት ያለማቋረጥ ሲጠየቅ የነበረ መጽሓፍ ስለነበረ ነው። በ2011 (እ.አ.አ ) ለጉብኝት በሄድኩም ጊዜ የሚያውቁኝ ሰዎች የጠየቁኝ ስለጤንነቴ ሳይሆን ስለዚሁ መጽሓፍ ነበር። ከሓዋርያው ጳውሎስ ቀጥሎ እግዚአብሔር በኃይል ተጠቅሞበታል የሚባለውን ይህን የእግዚአብሔር አገልጋይ ታሪክ በማንበብ ብዙዎች ተባርከዋል። በርግጥም ያ መጽሓፍ ብዙዎችን ነክቷል። 
ብዙዎችን ነክቷል ያልከውን እስኪ በምሳሌ አብራራልን?
ገና አገር ቤት እያለሁ የስርጭቱ ፍጥነት የመጽሓፉን ተወዳጅነት ያጎላ ነበር። ያነበቡትም ብዙ እንደተጠቀሙበት በአካልም በጽሑፍም ነገረውኛል። በተለይ ከዝዋይ ማረሚያ ቤት የደረሰኝ ደብዳቤ መቼውንም የምረሳው አይደለም። “መጽሐፉን እግኝቼ በማንበቤ በሕይወቴ ትልቅ መነቃቃት ሆኖአል። በአንድ ወቅት አማኝ ነበር። ግን በመሐሉ ልቤ ከጽድቅ ተንሸራተተና በድካም ስመላለስ ወንጀል ፈጽሜ ነው የታሠርኩት። አሁን ጌታ ከዚህ እንዲያወጣኝና እድሜ ልኬን እንዳገለግለው እየጸለይኩ ነው” የሚል ነበር። ወደአሜሪካ ከመጣሁም በኋላ ብዙዎች ስለመጽሐፉ ወሬ እንደሰሙ ግን ለማግኘት እንዳልቻሉ አንስተውብኛል። አንደኛ ሚዜዬን ጨምሮ በርካቶችም አገር ቤት እንዳነበቡትና እንደጠቀማቸው ነገረውኛል።
በቀደም ዕለት እንኳ ለአገልግሎት የጋበዘችኝ መጋቢ ለጉባዔው ስታስተዋውቀኝ እንዲህ ብላ ነበር። “ከዓመታት በፊት አንድ መጽሓፍ አንብቤ ሕይወቴ ተቀይሯል። ያንን ከቧንቧ ጠጋኝነት እስከታላቅ የእግዚአብሔር አገልግሎት የተሰኘ መጽሐፍ የተረጎመው ወንድማችን ዛሬ የእግዚአብሔርን ቃል ያካፍለናል”። ምስክርነቶቹ ብዙ ናቸው፤ ግን ጥቂቶቹን ተናገርኩ።
እንኳን ደህና ተመለስክ እንበልህ?
እንኳን ደህና ቆያችሁኝ ለማለት አላመነታም!
 
  “መመለሻዬ ደረሰ!” በሚል ከምስክር ብርሃኑ (ዋሽንግተን ዲ. ሲ) ጋር ያደረግሁት ቃለ ምልልስ 

Friday, March 13, 2015

ፈቃድ፣ ፈቃድ፣ ፈቃድ


“ከሁሉ በላይ ፈቃዳቸውን ማሸነፍና እንዲታዘዙ ማስተማር ነበረብኝ።   ለምንና እንዴት የሚለው እንዲገባቸው ማድረግ የጊዜ ጉዳይ ነው።   በመስማት ችሎታቸው ልክ በዝግታ መማር ይኖርባቸዋል።  ነገር ግን መታዘዝን መማራቸው ወሳኝ ነው። ያን ቶሎ መማራቸው እጅግ  አንገብጋቢ ነው።” 
“አዎን የልጆችን አመለካከት በቅጡ ለመቅረፅ ዋናው ጉዳይ አስቀድሞ ፈቃዳቸውን ማሸነፍና እንዲታዘዙ ማለማመድ  ነው። ግን ደግሜ ልበለውና እስኪገባቸው ጊዜ ይወስዳል፤ እናም እስኪለምዱት ድረስ ቀስ በቀስ ሊከናወን ይገባዋል።  ፈቃዳቸውን ማሸነፍ ለነገ የሚባል ጉዳይ ሳይሆን በተቻለ መጠን ፈጥኖ ሊከወን የሚገባው ወሳኝ ተግባር ነው።   ለምን ከተባለ በጊዜ ተግሣጽ ካላገኙ በቀር ግትሮችና ጠማሞች ስለሚሆኑ ያን ለማስወገድ ይቸግራል።   ኋላ የግድ መስተካከል ያለበት የዐመል ችግር ልጆቻቸው ላይ እያዩ ቸል የሚሉ ወላጆችን ጨካኝ ነው የምላቸው። አንዳንዶቹም ልክ እንደስፖርት ሥርዓትን ለልጆች በኋላ ማስተማር ይቻላል ብለው የሚያምኑ ደካሞች ናቸው።”
   “ የወደፊት ኑሮአቸውን አመላካች ነውና ይህን ጉዳይ እንደዋዛ አንሥቼ ላልፈው አልፈልግም። ፈቃድ ለኃጢአትም ይሁን መከራ በር ከፋች ነው።  እምነትም እኮ ቢሆን የራሳችንን ሳይሆን  የእግዚብሔርን ፈቃድ ማድረግ ነው።  ልጆችን ወደፍጹም ፈቃድ ለማምጣት ስንተጋ  መፍቀዳችን ውጤት አልባ መከልከላችንም ያለፍሬ ሊሆን አይችልም። መንግሥተ ሰማይና ሲዖልም የፍቃድ ውጤቶች ናቸው። እናም የልጆቹን ፈቃድ ለማስገዛት የሚሠራ ሰው የእግዚአብሔር አጋር ነው። ነፍስን ለማደስና ለማዳን ይሠራልና።     በአንፃሩ የልጆቹን ፈቃድ መረን የሚለቅቀው ሰው ከዲያብሎስ ጋር ወግኗል። በልጆቹ ዐይን ፊት እምነትን የማይጨበጥ መዳንንም የማይሞከር ያደርገዋል። ሳይታወቀው ልጆቹ በነፍስና በሥጋ የጠፉ እንዲሆኑ እየተጋ ነው።”


ሱዛና ዌስሊ ለልጇ ጆን ከጻፈችው ደብዳቤ

Tuesday, March 3, 2015

ራስህን አድን (የመጨረሻው ክፍል)!

 

በክፍል አንድ ከአንድ እስከአስራስድስት በክፍል ሁለት 17-32  በክፍል ሦስት ደግሞ 33-47 አስፍረናል። እነዚህ 48-64 ያሉት ናቸው።

49  ለሌሎች ሰብከህ ራስህ የተጣልህ እንዳትሆን ሥጋህን ጎስም (1 ቆሮ. 9:27)
50   ለእግዚአብሔር እንደሚጠየቅ ሰው ሆነህ ነፍሳትን ፈልግ።
51  ለመዳን የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ለሰሚዎችህ  ታስተምር ዘንድ ትጉ ተማሪ ሁን።
52   በሃብታሞች አትደለል።
53  ሆችን ፍላጎት ለማወቅና እነርሱን ለማስተማር የተለየ ትኩረት አድርግ።
54 ለኃጢአት እንድታመቻምች የሚያደርግህ ከሆነ በለጋሾች አትደለል።
55   አብላጫ ቁጥር ባላቸው አድማጮ ፊት ከበሬታን ይነፍግሃልና በአደባባይ ለማኝ መስለህ አትታይ።
56  ልቅ፤ ስሕተትና ጎጂ የሆነ ነገር ላለመናገር ይልቁንም አፍህን ለመዝጋት ትልቅ ጥንቃቄ አድርግ።
57 በጎ ሕሊናህን እንዳታጣ፤ ቅዱሱን መንፈስ እንዳታሳዝን፤ ሕዝብህም ባንተ ላይ ያለውን አመኔታ እንዳታጣና የእግዚአብሔር ሞገስ እንዳይርቅህ የመጋቢነት አገልግሎትህን እውነተኛና ነፃ አድርግ።
58 ለመንጋው ምሳሌ ሁን። ስብከትህ በኑሮህ ይገለጥ። መንፈስህና ድርጊትህ የበለጠ አስተማሪ መሆናቸውን አስታውስ።
59 ሰዎች እግዚአብሔርና ጎረቤታቸውን በፍቅር ሊያገለግሉ ይገባል ብለህ ከሰበክህ አንተም ያንኑ አድርግ። ለደሞዝ ብቻ የምትሠራ የሚያስመስልህን አካሄድ ከአንተ አስወግድ።
60 ሕዝብህን በፍቅር አገለግል። እነርሱም በተራቸው ስለ አገልግሎትህ ገንዘብ ሳይሆን ፍቅርን እንዲክሱህ አበረታታቸው። ይህ ሁላችሁን ያነቃቃልና።
61 ዓለማዊ የሆኑ ጮሌዎችን ሊያነሣሣ አክሎም ንቀትን ሊያጭር ስለሚችል ለአንተና ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውል ገንዘብ ሊለምን የተዘረጋ እጅህ ይሰብሰብ።
62 በተለይ ተባብሮ ነፍሳትን ለክርስቶስ ለመማረክ በሚመች ጊዜ ከሻይ ግብዣዎች፣ ለመስሕብ ብቻ ከሚደረጉ ገለጻዎችና እዚህም እዚያም ከሚደገሡ ጥሪዎች ራስህን አቅብ። የእግዚአብሔርን ሥራ ለመሥራት ስትጸልይና ስታቅድ  አንዳንድ ከዓለማዊነት ያልራቁ አባሎችህ ለድግስ ይጋብዙህ ይሆናል፤ አትሂድ። እነርሱ ክበብ ውስጥ ከገባህ በጸሎትህ ሽንፈትን መከናነብህ አይቀርም። ክፉው ወደዚህ መሥመር ሊመራህ እንደሚሞክርም አትጠራጠር።
63 አትታለል። እንዲህ ዓይነቶቹን ግብዣዎች በእንዲህ ዓይነቱ ጊዜ በመቀበልህ ጉባዔው በመንፈሳዊ ሥልጣን ከፍ አያደርግህም። ስዎች ደስ ሊሰኙ ከወደዱና ወቅቱ ለግብዣ አመቺ ከሆነ ለሃይማኖታዊ ስብሰባም አመቺ መሆን አለበት።  ተፅዕኖህ ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር ቤት ለመሳብ መዋል ሊውል ይገባል።
64  ክርስቶስን እወቀው። በየዕለቱም በእርሱ ኑር!
 .