ሰሞኑን ዋነኛው ወሬ ወንድ ልጅ ተወለደ አዲስ ንጉሥ ወደ ምድር
መጣ የሚል ሆኖ ነው የሰነበተው። ይባስ ብሎ ልጁ የተወለደው የቢቢሲ መቀመጫ ከሆነው እንግሊዝ አገር ሆነና የዜና ሁሉ ቁንጮ ሆኖ
አረፈ። ግን እኮ ከ2000 ዓመታት በፊትም እንዲሁ በምድራችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተባለ ሌላ ንጉሥ ተወልዶ ነበር። እናም የሁለቱን
ነገሥታት ልደት ለማነፃፀር ወደድኩ። ለዚያ የገፋኝ የመጀመሪያ አሳብ የተወለዱበት ሥፍራ ነው። እንደሰማነው የእንግሊዙ አልጋ ወራሽ
የተወለደው በለንደን የቅድስተ ማርያም ሆስፒታል ሲሆን ኢየሱስ ግን ዛሬ በካርታ ላይ ለማመልከት በሚቸግር በረት ውስጥ እንደተወለደ
በግርግምም እንደተኛ ልብ ይሏል። በዚሁም መሠረት ኢየሱስን ታላቁ ንጉሥ የለንደኑን ሕፃን ደግሞ ትንሹ ልዑል እያልኩ እጥር ምጥን
አድርጌ እንደሚከተለው ተነተንኳቸው።
ዜናው
ሓምሌ 22 ከቀኑ 10 ሰዓት ከሃያ ደቂቃ ላይ የተወለደው ሕፃን
እርሱም ትንሹ ልዑል በጾታው ወንድ መሆኑን ለማብሠር የለንደንን ትልቅ መመልከቻ መንኮራኩር ጨምሮ ከተማይቱ ሁሉ በሰማያዊ ብርሃን
ደምቃ አምሽታለች። ለክብሩም ስልሳ ሁለት ጊዜ መድፍ ተተኩሷል። “ሕፃን ተወልዶልናል ፤ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል” ብሎ ነቢዩ ኢሳይያስ
ከአራት መቶ ዓመታት በፊት የታላቁን ንጉሥ ልደት አውጆ ነበር። በታሪክ ታይቶና ተሰምቶ በማያውቅ ሁኔታ ድንግሊቱ ፀንሳ አማኑኤልን
ወለደች። ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው ይለናል የመጻሕፍት ሁሉ መጽሐፍ የሆነው ሕያው የእግዚአብሔር ቃል። ዜናውንም
ወደምድር ያመጡት ጋዜጠኞች አልነበሩም። መላእክት ናቸው። ለተናቁት በግ ጠባቂዎች ይህንኑ ሲነግሩአቸው “ለምድር ሁሉ የሚሆን የምሥራች”
የሚል ግሩም ርዕስ ሰጥተውታል። በዙፋኑ ዙሪያ የሚዘምሩት የእነዚሁ መላእክት ዜማ ወደሰው ልጆች ጆሮ የገባውም ያኔ ነበር።
አቀባበል
እንግሊዝን የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዴቪድ ካሜሩን ዛሬ የታላቅ
ደስታ ቀን ነው ሲሉ በይፋ ተናግረዋል።በትንሹ ልዑል መወለድ ደስ የተሰኙ ነገሥታት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የአውስትራሊያው ጠቅላይ
ሚኒስትርና የካንትረበሪውን ሊቀ ጳጳስ ጨምሮ በርካቶች ከዓለም ዙሪያ የደስታ መግለጫ መልእክት አስተላልፈዋል። “ሁላችንን በአንድ
የሚያሰባስብ ከዚህ የተሻለ ታሪካዊ ክስተት ከቶ የት አለ” ስትል ከሆስፒታሉ ደጃፍ ከተኮለኮሉት አንዷ በመፍነክነክ የተናገረችው
የብዙዎችን ስሜት ይወክላል። የግብዣው ወጪ ብቻ 400 ሚሊዮን ፓውንድ ይገመታል ነው ያሉት የሒሣብ ዐዋቂዎች። ወደታላቁ ንጉሥ ስንመለስ
ግን ጥቂት ምሥጢሩ የገባቸው ጠቢባን ስጦታ ያምጡለት ታታሪዎቹ እረኞችም በመደነቅ ይጎብኙት እንጂ መላው ዓለም ስለንጉሡ መወለድ
ደንታ አልነበረውም። ከመጀመሪያውም እንኳን የማዋለጃ ሥፍራ ማደሪያም አላገኘም። ስለዚህ ከከብቶች ጋር በአንድ በረት እንደታጎር
ሆኗል። እዚያው ሳለም የልደት በዓል ሳይሆን ንጉሡና ባለሥልጣናቱ ሳይዉሉና ሳያድሩ የሞት ድግሥ አዘጋጅተውለታል። በወጣትነት ዘመኑ
የሦስት ዓመት ተኩል አገልግሎቱን ጨርሶ በስቅላት ቢገደልም ቅሉ ሞት የተፈረደበት ግን ገና ከመወለዱ ነበር።
ስማቸው
ልዑል ዊልያምና ባለቤቱ ኬት ስለልጁ ስም ሲጠየቁ “እያሰብንበት
ነው ፋታ ስጡን” ነበር ያሉት። ልጁ ከተወለደ በኋላ ተማክረው ያበጁትን ስም አሳውቀዋል። እናም ትንሹ ልዑል የተከበሩ ግርማዊ የኬምብሪጅ
ልዑል ጆርጅ አሌክሳንደር ሊዊስ ተብሎአል።ወደታላቁ ንጉሥ ስንዞር ግን አሁንም ከመወለዱ ብዙ መቶ ዓመታት በፊት “ስሙም ድንቅ መካር ኀያል አምላክ የዘለዓለም አባት የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል” ብሎታል ነቢዩ ኢሳይያስ። ወደእናቱ የመጣው መልአክም
ስሙ ማን እንደሚሆን ተናግሮአልና ማርያምና ዮሴፍ መማከር አላስፈለጋቸውም።
ንግሥናቸው
የትንሹ ልዑል ቅድመ አያት ንግሥት ኤልሣቤጥ ለ61 ዓመታት ዙፋኑን
እንደተቆናጠጡ ናቸው። አያቱ ያንን ወንበር ሲጠብቅ አረጀ። ቀጥሎ ደግሞ አባቱ አለ። ያንን ሁሉ ተከትሎ ነው አዲሱ ሕፃን በአራተኝነት
ለንግሥና የተሰለፈው። ከቀናው ከእንግሊዝም አልፎ ካናዳ፤ አውስትራሊያና ጃማይካን ጨምሮ በአስራስድስቱ የኮመንዌልዝ አገሮች ላይ
ንግሥናው ይጸናል።ምናልባትም ሳይነግሥ ሊሞት ይችላል። በአንፃሩ የኢየሱስ ንግሥና ከዘመናት በፊት የጸና ነው። ወደምድር ሲወርድም
ንጉሥ ነበር። የገባቸው “ሆሣዕና በአርያም” ብለውና ዘንባባ አንጥፈው በሆታ ተቀብለውታል። እርሱ ንጉሥ ብቻ ሳይሆን የነገሥታት
ንጉሥና የጌቶችም ጌታ ነው። የተከበሩ ንግሥት ኤልሳቤጥን እና የልጅ ልጃቸው የሆነው ትንሹን ልዑል ጨምሮ ታላላቆች ሁሉ በእግሩ
ሥር ወድቀው ይሰግዳሉ።
መደምደሚያ
ቤኪንጋም ቤተመንግሥት አንድ ልዑል ተጨመረልን ተብሎ ፌስታው ቀልጧል።
እንኳን ደስ ያላቸው። በጥቅሉ ግን ይህ ዓለም ከታላቁ ንጉሥ ወደ ምድር መምጣት ይልቅ በትንሹ ልዑል መወለድ የተመሰጠ ይመስላል።
የታላቁን ንጉሥ ልደት ዘክር ሲባልም የራሱን ስጦታ ለመለዋወጥ ሚሊዮኖችን የሚያባክን ጥበብም የጎደለው ሆኗል። ገናን ጠብቆ ንግዱን
ያጧጡፋል፤ ዳንኪራ ይመታል። ኢየሱስ ከ2000 ዓመታት በፊት በቤተልሔም ተወለደ ይላል። አንተስ ያንን ሰምተህ ዳግም ተወልደሃል
ሲባል ግን ሰማይና ምድሩ ይዞርበታል። በርግጥም የዞረበት ዓለም ነው
ጃል!