ጊዜ ባገኝ፤
የማደርገውን አውቃለሁኝ፤
የመጻሕፍቴ ገጾች ወደቅን እስኪሉኝ፤
አነባቸው ነበር እየደጋገምኩኝ።
ጊዜ ባገኝ
እጽፍ ነበር በርካታ ደብዳቤዎች፤
ያልመለስኳቸውን ለብዙ ሳምንቶች፤
ለብዙ ብዙ ሰዎች።
ጊዜ ባገኝ
እከፍል ነበር የስልኬን ወረት፤
ያጠራቀምኩትን ለሳምንታት፤
ደግሜም አልዘገይ በውነት።
ጊዜ ባገኝ
ሕይወቴን እቃኛለሁ በዚያ፤
ጊዜ ይኖረኝ ዘንድ መግባቢያ፤
ከሚስቴ ጋር መቀራረቢያ።
ጊዜ ባገኝ
ግሩም የደስታ ሕልም፤
ከወር ከዓመት ከአስር ዓመት በኋላ ወይም፤
ግን ይህን መጨረስ አልችልም፤
ምክንያቱም ጊዜ የለኝም።
ገጣሚው ቶማስ ኤል ሜሰን እንዳለው እኔም ጊዜ ሳገኝ እያልኩ ያዘገየሁት አንድ አሳብ ነበረኝ። ይኸውም አንድ የጽሑፍ ሠሌዳ( Blog) ከፍቼ አንዳንድ አሳቦችን ከናንተ ጋር መካፈል ነው። ዛሬ ሞላልኝ። ዳር ላይ ቆሜ ሳመነታ “ትችላለህ” ብላ ወደዚሁ የገፋችኝን ብሌንን ላመሰግን ይገባኛል። ይህንኑ የጽሑፍ ሠሌዳ “ከአለፍ አገደም” ብዬ ሰይሜዋለሁ። ምክንያቱ አሁንም የጊዜ ጉዳይ ብቻ መሆኑ ይሰመርበት። ከተማሪነቴ ከሙሉ ጊዜ ሥራዬ አልፎ አልፎ ከምሠራው የማስተርጎም ሥራ ቤተሰብ ከማስተዳደሩና መጻሕፍትን ከማዘጋጀቱ ባሻገር መሆኑ ነው። ስለሆነም ከአለፍ አገደም እዚሁ እንገናኝ! በአጋጣሚ በዚህ ያላካተትኳቸውና ቢያነቡ አይጠሉም የምትሏቸው ቢኖሩ መልዕክቱን አድርሱላቸው ስል በትሕትና እጠይቃችኋለሁ።
ወዳጃችሁ
ዓለማየሁ ማሞ
http://alemayehuwrites.blogspot.com/