የሰባኪዎች ልዑል ተብሎ የሚጠራውን ቻርልስ ስፐርጅንን ማስተዋወቅ
አያሻኝም። የዚህ ሰው ጸሎት ከስብከት ያልተናነሰ በመሆኑ ብዙዎች አብረውት ከመጸለይ ይልቅ የሚለውን በማስታወሻቸው ለመጻፍ
ይፍጨረጨሩ ነበር። ያንን ለማርገብ ሲባል በአንድ ምሽት አገልግሎት መክፈቻ ላይ ያቀረበው ጸሎት ተመዝግቦ ለመዘክርነት ተቀመጠ።
እንዲህ ነበር።
“ጌታ ሆይ እባክህ ሕዝብህን አድን፤ ሕዝብህን አድን። ጸሎቴ በፊትህ
መሆን እንደሚገባው እንዳልሆነ አምናለሁ። በጸጋህ እርዳኝ። በሰጠኸኝ ዕድሜና ኃይል እንደሚገባ እንዳልሰበክሁ ግልጽ ነው። ጌታ
ሆይ በእኔ በደል ሌሎችን ቸል አትበል። ሕዝብህን አድን። በእረኛው ጥፋት መንጋውን አትምታ። ይቅር በላቸው አባት ሆይ፤
ምሕረትህ ከእነርሱ ጋር ትሁን።
ይቅርታን ያላገኙ ብዙዎች በዚህ አሉ። ይድኑ ዘንድ ምን ያህል
እንደደከምን አንተ ታውቃለህና አልዋሽም። የሰው ልብ ጠንካራ ነው አባት ሆይ፤ ነፍሱም እንደ ብረት ነች። ደምና ሥጋ ሰውን
ሊለውጥ አይችልም። መጋቢው ተስፋ ያደርጋል፤ አገልጋይህም ያምናል። ግን ሁለቱም ማዳን አይሆንላቸውም። ጌታ ሆይ አንተ ግን
በኃይልህ ትችላለህ። አንተ ካልሳብካቸው ሊከተሉህ አይችሉም።
የእሥራኤል አምላክ ሆይ በዚህ ዓመት ደግሞ ይህችን ቤተ ክርስቲያን
እርዳ። ሕዝብህን በጸሎት ባርክ። ሥጋን በመንፈስ ይገድሉ ዘንድ አበርታቸው። በዚህ ብቻ ሳይሆን በሁሉ ሥፍራ ኢየሩሳሌምን
ለምስጋና እስክታደርጋት ድረስ አንዳያርፉ እርዳቸው። ጸሎትን ጨምር ጌታ ሆይ።
የምንጮኸውና የምናነባው ስለ ቤተ ክርስቲያንህ ብቻ አይደለም። ስለ
ዓለም ሁሉ እንጂ። በከንቱ እንደማልደክም አልተናገርኸኝምን? ለባሪያዎችህስ ይህንኑ አላልክምን? እንግዲያውስ በሰዎች መዳን
አጥግበን። “ዝናብና በረዶ ከሰማይ እንደሚወርድ ምድርን እንደሚያረካት ታበቅልና ታፈራም ዘንድ እንደሚያደርጋት ዘርንም ለሚዘራ
እንጀራንም ለሚበላ እንደሚሰጥ እንጂ ወደ ሰማይ እንደማይመለስ ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ይሆናል” ተብሎ እንደተጻፈ ቤተ
ክርስቲያንህን አስፋ። አስፋልን ጌታ ሆይ።
ዛሬም በዚህ ምሽት ቃልህ በከንቱ አይመለስ። ባሪያህ በቅን ልብ
በፍቅርና በርኅራኄ እንዲሰብክ እርዳው። መንፈስ ቅዱስ ሆይ ና! ያላንተ ምንም ልናደርግ አንችልምና በትኅትና እንጋብዝሃለን።
በአብርሐም፤ ይስሐቅና ያዕቆብ ላይ የነበርክ የከበሩ ሕልሞችን ለሰዎች ትንቢትን ለነቢያት የሰጠህ በሐዋርያትና በቀደመችው ቤተ
ክርስቲያን ላይ ያደርክ ታላቁ የእግዚአብሔር መንፈስ ሆይ በዚህች ምሽት ከእኛ ጋር ሁን። ይህች ምድር ትናወጥ። ነፍሳትም
ልባቸውን ከፍተው የከበረውን ቃል ይስሙ። ሥጋ ለባሽ ሁሉ አንተን በማወደስ ሐሤት ያድርግ። ለዘላለም ለሚኖረውና ከፍ ላለው
ለአብ፤ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ክብር ይሁን፤ አሜን!”
እኛም አሜን እንበል.....
No comments:
Post a Comment