እዚሁ ሲልቨር ስፕሪንግ
“አንድ ልብ” በሚል መሪ አሳብ በቅርቡ የተካሄደ ኮንፍራንስ ነበር።
በነሐሴ 8 2015 ቅዳሜ ቀን ለወራት ያልታየው ዘማሪ ድምፅ ማጉያውን ጨበጠ። ታዳሚዎቹም ተነሥተው በጭብጨባ
ተቀበሉት።
እንግዲህ በሰሜን አሜሪካና
አካባቢው የሰሞኑ ዐበይት ወሬ “ተከስተ ዳግም ተከሰተ” የሚል ሊሆን ነው። መቼም ወሬ ከነሁሴን ቦልት ፈጥኖ ይሮጣልና ደግሞ ዓለምን
ሊያደርስ ነው። ያንን ተከትሎ ደግሞ ዝርወተ ኢትዮጵያውያኑ እንደ ጨው በተበተኑበት ሁሉ “መቼ፣ እንዴት፣ ለምን፣ የት እና ወዴት”
የተሰኙ ማብቂያ የለሽ ጥያቄዎች በዘማሪው ዳራና መፃዒ ዘመን ዙሪያ በማኪያቶ ሊወራረዱ ነው።
አስቀድሞ ያንን ጥም ለመቁረጥ
ይህችን አጭር መረጃ መልቀቁ ሙያዊና ወንድማዊ ግዴታዬ ሆኖ አገኘሁት።
ዝርዝሩን እንደወረደ...
መረጃው እንደደረሰኝ ፓስተር
ተከስተ ጌትነት ወደሚያገለግልባት የፀጋ ቤተ ክርስቲያን ስልክ መታሁ። መጋቢ መስፍን አስፋውን አግኝቼ ስላለፉት 12 ወራት ዋና
ያለውን እንዲነግረኝ ጋበዝኩት። በየሳምንቱ እየተገናኙ ሲጸልዩና ሲመካከሩ እንደነበር በግልጽ አስረዳኝ። አሁን ወደ መድረክ ስለመመለሱ
የምሰማው ወሬ እውነት ነው እንዴ አልኩና ለመስማት ተዘጋጀሁ። አንደበተ ርትዑ ወዳጄ ለመልሱ አላመነታም። “አዎ” አለኝ “አዎ፤
በሦስት ዓይነተኛ ምክንያቶች ወደ አገልግሎቱ ልንመልሰው ነው። በመጀመሪያ በውድቀቱ ተፀፅቷል። በሁለተኛ ደረጃ የጣልንበትን የአንድ
ዓመት እገዳ ያለምንም ማንገራገር ጨርሷል። በመጨረሻም በነዚህ ወራት ከእኛ ሳይለይ የአባልነት ግዴታውን ተወጥቷል። ስለተደረገለት
ክትትልና ስለተቀበለው የተሐድሦ ትምህርት ማወቅ ከፈለግህ ግን በዚህ የረዱንን ፊላደልፊያና ሳንፍራንሲስኮ ያሉ ሁለት መጋቢዎች ማግኘት
ይኖርብሃል።”
በማግሥቱ ደግሞ ስልኬን
ወደ ካሊፎርኒያ አዙሬ ፓስተር ተስፋዬ ተሰማን አገኘሁት። በርግጥም ይህ ጥያቄ ቀርቦለት ነበር። “በመካከላችን ያለውን ርቀት በማጤን
ይልቁንም በሁለቱ መካከል ለረጅም ጊዜያት የተገነባውን የአማካሪና መካሪ ዝምድና በማጤን ፓስተር እንዳልክ ጉዳዩን እንዲይዘው ሁላችን
ተስማማን ” ብሎኛል። ይህ ውይይት የሦስት ሰዓት መንገድ ወደሚርቀን
ፓስተር እንዳልካቸው ሣሕሌ መለሰኝ። የአራት ኪሎው ወዳጄ ደግሞ ሁለቴ ያቃጨለውን ስልክ አንሥቶ መለሰልኝ።
እሱም በበኩሉ ጥያቄዬን
በጥሞና ካደመጠ በኋላ “አዎን የረጅም ጊዜ ትውውቃችን፣ በበዓለ ሲመቱ
ላይ መገኘቴና ይልቁንም ቤተ ክርስቲያናቸው ከጣለችብኝ አደራ የተነሣ ብዙ ጊዜ አብሬው አሳልፌአለሁ። ዝርዝሩን ግን ለነርሱ ካቀረብኩት
ሪፖርት ማግኘቱ ይቀልሃል”አለና ስልኩን ሳንዘጋው በፊት ደብዳቤውን ከፊላደልፊያ ኢሜል አደረገልኝ።
ወዲያውኑ ከፍቼ አነበብኩት።
በፊላደልፊያ የኢትዮጵያ
ወንጌላዊት ቤ/ክ ዋና መጋቢና የኮምፓስ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር የሆነው እንዳልካቸው የላከው ደብዳቤ ይዘትም መስፍን ከነገረኝ ጋር
የሚታረቅ ነው። ስለዚህ ዋና ዋና ቁም ነገሮቹን እንደሚከተለው ጨምቄአቸዋለሁ።
ከጥቅምት ወር 2014 ጀምሮ በራስ ተነሣሽነት ሲመክረውና ሲጸልይለትም ቆይቷል። የካቲት 15 2015 ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱ
በይፋ ደብዳቤ የፓስተሩን ርዳታ ጠይቃለች። ይህኔ ደግሞ ባለቤቲቱንም
በመጨመር በርካታ ጊዜያት እያገኛቸው አደራውን ለመወጣት ይተጋል። ተሳክቶለትማል።
እንደ ደብዳቤው ከሆነ 38 ሰዓቶችን ለተሐድሦ ትምህርት ምክርና ጸሎት የተጠቀሙ
ሲሆን ዘጠኝ ለሚያህሉ ሰዓቶች ደግሞ እንዳልክና ተከስተ የምሥራችን (የተከስተ ባለቤት) ጨምረው ተመካክረዋል። አንድ ጊዜ ባለጉዳዩ
ወደ ፔንሲልቬኒያ ከመሄዱ በስተቀር ቀሪውን ጊዜ ባለአደራው ወደ ሜሪላንድ መመላለሰ እንደነበረበትም ደብዳቤው አብራርቷል። በነዚህ
ጊዜያት ያተኮሩባቸውን አራት ዋና ጉዳዮች አማካሪው ዘርዝሮ የጻፋቸው ሲሆን ፍሬ ነገራቸው ይህንን ይመስላል።
ሀ) ጥፋትን ማመን፣ መናዘዝና የእግዚአብሔርን ይቅርታ ማግኘት ለ) ውድቀቱን
ላለመድገም በመከላከል ላይ ያተኮረ ትምህርት ሐ)በመሃሉ ቅድሚያ በመስጠት
የተጎዳውን ትዳር መጠገን፣ በታቀዱ የግል ጊዜዎች በመታገዝ ፍቅርን ማሳደግ መ) ከአገልግሎቱ ዘዋሪነትና ተፈላጊነት አንጻር ሊወሰድ
የሚገባው ጥንቃቄ የሚሉ ናቸው።
ፓስተር እንዳልካቸው ከሰደደው
ከዚሁ ሁለት ገጽ ደብዳቤ ውስጥ የግል አስተያየቱንም ጨምሯል። በዚሁም መሠረት የንስሐ ቆይታውን በአጥጋቢ ሁኔታ እንደፈጸመ ይልቁንም
የተሰጠውን አገልግሎት(ትምህርት፣ ምክርና ጸሎት) በብዙ ትኅትናና ፈቃደኝነት ተከታትሎ እንደጨረሰ ካወሳ በኋላ “ቤተ ክርስቲያኒቱ ምስክርነቴን ተቀብላ ...ቀሪ እርምጃዎች ካሉ በማስፈጸም
...አገልግሎቱን የሚጀምርበትን ሁኔታ እንደምታመቻች እምነቴን እገልጣለሁ”
በማለት ይህ ምኞቱና ጸሎቱ እንደሆነም አበክሮ በመግለጽ ደምድሟል።
ቤተ ክርስቲያኗ በበኩሏ
በዚሁ የተስማማች ቀሪ ሥራዋንም ያጠናቀቀች መሆኑ እየታየ ነው። ከላይ የጠቀስኩት የመጋቢው እማኝነት እንዳለ ሆኖ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ነሐሴ 29 ይህንኑ የሚያውጅ ስብሰባ አዘጋጅታለች። ያኔ ቦስተን ስለምሆን
ለእናንተ አንባቢዎቼ የዐይን ምስክርነት አይኖረኝም። እናም ሰበር
ዜና ይዤላችሁ መጣሁ።
እንግዲህ ተኬ ዳግም ሊከሰት
ነው። በዓመታት መካከል በአገልግሎቱ ብዙ ተጠቅመናል። በዝማሬዎቹም ተባርከናል። አሁን ሲመለስ የመጀመሪያ ዜማው ምን ይል ይሆን? እንደኔ ግምት “ጠላቴ ሆይ ደስ አይበልህ፤ ብወድቅ እንኳን እነሣለሁ” ሳይሆን
አይቀርም።
በነገራችን ላይ ተከስተን
እወደዋለሁ!