Tuesday, June 7, 2016

ፈርጦች ሲገመገም!

ቅንት በ‹‹የሕይወቴ ፈርጦች›› መፅሐፍ ላይ
አቅራቢ ስሜ ታደሰ
ደራሲ ዓለማየሁ ማሞ
የገፅ መጠን 270
ሕትመት በርሆበት አታሚዎች
ዘመን 2007 ዓመተ ምህረት
የዛሬ ንባቤ በ‹‹የሕይወት ፈርጦች›› መፅሐፍ ላይ ያተኮረ ይሆናል፡፡መፅሐፉ 270 ገፆችን በመሸፈን በዓለማየሁ ማሞ የተሰናዳ ነው፡፡ ይህ ዝግጅት የአዘጋጁ ግለ ታሪክ(Auto biography)ሰለሆነ ገለፃዎቹ የእርሱን ሀምሳ አመታት ያልደፈኑ የኑሮ ዘይቤዎቹ ከሆኑት ውስጥ ዋና ዋና ያላቸውን በመግለፅ እንድናነበው ይጋብዛል፡፡ይህንንም በውስጥ ገፆቹ High lights of My life ወይም የሕይወቴ ፈርጦች በማለት ገልፆታል፡፡
***
ዓለማየሁ ማሞ ያዘጋጀውን ይህን መፅሐፍ መቃኘት ከመጀመሬ በፊት ‹‹የሥነ ፅሑፍ መሰረታውያን›› አዘጋጅ ዘሪሁን አስፋው ‹‹የሥነፁሁፋዊ ሒስ አስፈላጊነት››ን የገለፀበትን ማብራሪያ የዚህ ስራ መግቢያ ላድርገው፤-ዘሪሁን አስፋው‹‹ ሥነፁፋዊ ሒስ ለደራሲው፣ለአንባቢው፣እና በአጠቃላይ ለስነፁሁፋ ያለው አስፈላጊነት እና የሚሰጠው አገልግሎት ከምንም በላይ የላቀ ነው፡፡በአንድ ደራሲ ሥራ ላይ የሚደረግ ሥነፁፋዊ ሒስ የሥራውን ጥንካሬና ድክመት የሚያሳይ በመሆኑ ደራሲው ጠንካራ ገፅታዎችን በማወቅ በተከታይ ስራው ይበልጥ እንዲጠቀምባቸው፣ደካማ ገፅታዎቹን ደግሞ በመተው የማሸሻያ ነጥቦችን ሁሉ እንዲፈልግ ያግዘዋል፡፡…››በማለት ሒስ ለደራሲው፣ሊኖረው የተገባውን ጠቅም ያሳውቃል፡፡(የስነ ፅሁፍ መሰረታውያን ገፅ 357)
***
ዘሪሁን ‹‹የሥነፁፋዊ ሒስ ለሌላኛው ጥቅም ለአንባብያንም ጭምር ነው›› ይላል፡፡ ‹‹…ሐያሲው የሚሰጠው ትንታኔ የተደበቀውን የማውጣት፣አሻሚውን የመለየት፣የረቀቀውን የማቅለል፣እንዲሁም የተምሳሌቱን ትርጉዋሜ የመግታት ተግባር ስለሚፈፅም አንባቢው ስራውን ከበፊቱ በተሻለ ሁኔታ ሊረዳው ይችላል››.››በማለት የሁለትዮሽ ጥቅሙን ያመላክታል፡፡(የሥነፀሑፍ መሰረታውያን ገፅ 357 1992)፡፡
***
ይህን ምልከታ በማስቀደም በ‹‹የሕይወቴ ፈርጦች››ላይ ያስተዋልኩትን እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡በመሰረቱ ካለፉት አስር አመታት ወዲህ እየተዘጋጁ ለገበያ የቀረቡ ግለታሪኮች በቁጥር እየጨመሩ መጥተዋል፡፡ይህ የዓለማየሁ ማሞ ስራ ደግሞ ተቆጣሪ ሆኖ ሲመጣ ቁጥሩን በአንድ ከፍ ያደርገዋል፡፡
***
በዚህ ከፍታ ውስጥ ፀሐፊው ‹‹እንደ መርከበኛ በባሕር፣እንደ ጋዜጠኛ በምድር›በላበት መፅሐፍ በሚገኙት ዘጠኝ ምዕራፎች ውስጥ መነሻውን እትብቱ የተቀበረበትን ‹‹ቀበና-አዲስ ››አድርጎ መድረሻውን ‹‹አሜሪካ ዋሽገንተን ዲሲ›› በማድረግ የኑሮ ክትትሎሽን በወጉ ለመዳሰስ ጥረት አድርጉዋል፡፡
***
በአንደኛ መደብ‹‹እኔ›› እያለ የሚፅፍልን ባለታሪክ ራሱ፤- ስለራሱ ስለሚናገር እንዴት ሰው ራሱን እንደሚገልፀው፣ እንደሚገነዘበውም እንዲሁም እንደሚረዳው እየተገረምንና እየታዘብን ክትትሉን እንቀጥላለን፡፡
ይህ ደግሞ ሰውን ሰው ባሰኙት የጋራ ባህሪያት ላይ ሁሉንም ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ ‹‹…እድሜዬ ሀምሳ አልሞላም ›››››.. የሚለን ፀሐፊ ሀምሳ ብዙ አመታት መሆናቸውን አንባቢ በቅጡ እንዲረዳው በማድረግ ያስነብበናል፡፡ ይህም ሆነልኝ ከሆነብኝ፣ያላቸውን ውጣ ውረዶች፤- ሀዘን ከደስታ፣መርዶ ከብስራት፣ጋር ቀላቅሎ ሀምሳ ባልሞላ ውጤታማ ዕድሜው ውስጥ አካቶ ያጉዋጉዘናል፡፡
***
በመኖር ውስጥ ሰው መሰረታዊ ፍላጎቱን ለማሙዋላት የሚሆናቸውን መዋተተቶች ስለሚገልፅልን ቀጣዬ ሀምሳ አመትስ ምን ሊሆን ይችላል? ያስብለናል፡፡
እርግጥ ነው፤-እኔ ስለራሴ በተናገርኩ ቁጥር ሆን ብዬ ወይም ልብ ሳልለው በአንባቢ ግንዛቤ ውስጥ ራሴን በድፍረት ልከት እችላለሁ፤በዚህ ጊዜ ደግሞ በአንባብያን የደራሲው ያልታዩ ድካሞች መውጣታቸው አይቀሬ ነው፤ከዚህም የተነሳ ‹‹…ከማንም በላይ የማውቀው ራሴን ነው፤…››(የሕይወቴ ፈርጦች ገፅ 9) የሚለው ደራሲ በእርግጠኝነት ስለ ራሱ ያወቀውን ሲገልፅ በትንታኔው ራሱን በቅጡ ባለመረዳት የተላለፉ ሀሳቦችን በትረካው ውስጥ እንዲገኙ እድል ፈጥሮላቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ በማህበራዊ ሳይንስም ሆነ በቅዱሳት መፅሀፍት ገላፃ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ በመሰረቱ ‹‹ሰው በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ልዩ ፍጡር ነው፡፡ይህ ደግሞ በሐጢያት ምክንያት በሰው ዘንድ ያለው ሙሉ አቅም ተዛብቱዋል፡፡በአስተሳሰቡ፣በፈቃዱ፣በውሳኔው፣ሁሉ ላይ ሕፀፆች አሉት ፡፡ ‹‹ ሁሉ ሐጢያትን ሠርተዋል ፤የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎቸዋል፡…›› ሮሜ 3፤23
***
ከዚህም የተነሳ ፀሐፊው ‹‹ ከማንም በላይ የማውቀው ራሴን ነው፡፡›› የሚለውን ቃሉን የጎሪጥ መመልከት ተገቢ ነው፡፡በትዩዩ ‹‹የሕይወቴ ፈርጦች›› ፀሐፊ በመኖር የገጠሙትን የርሱን ጠንካራ ጎኖች በመደርደር ‹‹እኔ አምበሳው›› አላለንም ይለቁኑ ፍርሀቱን ነግሮናል፡፡ውድቀቱን አጫውቶናል፡የወጣትነት ፍላጎቱ ታግሎ በድግግም እንደጣለው አልሸሸገንም፡፡ይህ ደግሞ መፅሐፉን ጀምረን እስክንጨርስ ያልተቁዋረጠ መገለጫው ነው፡፡በጥንካሬው ይመዘገባል፡፡ በክርስቶስ ሆንኩኝ ብርሁን በራልኝ ባለማግስት ‹‹አሳ አጥማጅ ከነበርክ ስታኮርፍም እዚያው ወንዝ ዳር ነው የምትገኘው››(የሕይወቴ ፈርጦች ገፅ 214) የሚለውን አያያዥ አነጋገርበማንሳት ትቶት ወደነበረው ሕይወት በመመለስ ‹‹… እሱ ሲጠጣ ቆሞ ማየቱ አላስቻለኝም እናም ለእኔም ስጡኝ አልኩኝ‹… ዘፈንና ዳንሱንም ለመከለስ ፈለግሁ …ቁነጃጅቱም ቢሆኑ የሚያሳልፉ አልነበሩም ተያይዞ መውደቅ ብቻ ሲቀረኝ መዳራቱን ግን ዳር ዳር አልኩኝ…››(የሕይወቴ ፈርጦች ገፅ 214) በማለት ራሱን እንድንረዳው ያደርገናል፡፡ ይህም ሰው ሰው መሽተቱን ያመላክታል፡ግሩም ነው፡፡
***
የትኛውም ፀሐፊ መልክዕት ሳይኖረው እንደማይፅፍ ሁሉ ደራሲውም አንጉዋ መልክዕት በ‹‹የሕይወቴ ፈርጦች›› ውስጥ አለው፡፡ ያም በክርስቶስ ያገኘውን ድነት ማስተዋወቅ ነው፡፡ይህን ያስረዳበት አካሄድ ግን ችሎታውን ጠያቂ እና ቅድመ ዝግጅቱን በቅጡ አደራጅ እንደነበር ሥራው ያብራራል፡፡ መፅሐፈ አስቴር በውስጡ እግዚአብሔር የሚል ቃል ሳይኖረው የእግዚአብሔርን መለኮታዊ ሥራ እንደገለፀ ሁሉ ይህም ሊሰብከን ሳይፈልግ ግን አንጉዋውን ጉዳይ ከዳር አድረሱዋል፡፡ደራሲው ተነባቢነቱን ሳያሳጣ አንባቢውም ‹‹አውቄልሀሉ ታዲያ ምን ይጠበስ››ሳይል ንባቡን እንዲገፋበት የሚረዳ የአተራረክ ስልትን ተጠቅሙዋል፡፡ ይህኑኑ አንጉዋ ጭብጥ በየቦታው በትኖ ያደረጀዋል፡፡‹‹…በነገራችን ላይ ለዚህ ሥራ ትልቅ ውበት የሆነኝ ነገር ወደ ሕይወቴ የመጣው ታላቅ ብርሀን ነው፡፡…››(የሕይወቴ ፈርጦች ገፅ 10) ያለለት የድነት ሥራ ነው በተለያየ ቃና እስከ መፅሐፉ ዳርቻ ድረስ ያዘልቀዋል፡ ደራሲው ይህን ቅድሚያ የምሰጥለት ነው እሰካለለት ድረስ ለዚህ ቃሉ ታመኝ መሆኑ ያስመሰግነዋል፡፡
***
የደራሲው የቁዋንቁዋ አጠቃቀም ደግሞ የሚያስመሰግን ው፡፡ማንኛውም ደራሲ ተደራሲውን ሳያደናግር ለፃፈው መልክዕት አስተርጉዋሚ የሚፈልግበትን የአፃፃፍ መንገድን መከተል የለበትም፡፡ ግልፅ ፣ምጥን፣በተገቢው ቦታ ማብራሪያ መስጠት ፣ አላስፈላጊውን መተው፣ሥርዓተ ሰዋሰውን፣ስርዐተ ነጥቡን፣የአረፍተ ነገር አወቃቀሩን በአግባቡ በመስራት ለተደራሲ ማድረሱ ዓለማየሁ ማሞን በድጋሚ ያስመሰግነዋል፡፡እሱ በርካት መፅሐፍትን ከመድረሱ ፣ከመተርጎሙ የተነሳ እና በሌሎች በጎ ምክንያቶች የተነሳ ማንም ሊረዳው የሚችልን ግለ ታሪክ አስተላለፎአል፡፡
ዘሪሁን አስፋው እንዳስነበበው ሒስ ደራሲውን ይጠቅማል፤ ደካማ የመሰሉ ስራዎቹን በቀጣይ እርሞ እንዲጠነቀቅባቸው ያደርጋል፡፡››እንዳለ ሁሉ እኔም በ‹‹የሕይወቴ ፈርጦች›› ላይ በቅጡ ሊታረሙ ይገባቸዋል የምላቸውን ጥቂት ነጥቦች አንስቼ ልፈጽም፡፡
***
አንዱ፤- በታሪኩ ውስጥ ደራሲው እንቅፋቶች በተደጋጋሚ ገጥመውታል፡፡እነዚህን መቁዋቁዋም ያልቻለው የሚታደገው አቅም ያለው ሰው ስሌለው እንደሆነ በመደጋገም ይነግረናል፡፡ገፅ 84 ‹‹..ለምን ቢሉ ሰው አልነበረኝም›› ገፅ 97 ላይ ‹‹መመዘኛው አበልጅ፣የጡት ልጅ፣ምን ምን የሚል ስለነበር›››. ገፅ 105 ‹‹…ለምን ቢሉ ሰው አልነበረኝም›…›. ገፅ 259 ‹‹…በገጠመኜቼ ውስጥ በተደጋጋሚ እንዳነሳሁት ሰው ስላልነበረኝ ብዙ ነገሮች አምለጠውኛል…››ይላል ይህ ገለፃ ምን ያህል ትክክል ነው ?ሰው በማያስፈልገው አቅም የግለ ታሪኩ በላቤት ራሱን ማየት የሚኖርበት አቅጣጫ አልነበረም ወይ ?ሰው የለኝም የሚለው የነገራት መተርጎሚያ እንደ ሁነኛ ሰበብ አልሆነም ወይ ? በማለት መዝለቁ ተስፋዬ ‹‹ሰው ነው›› መደገፊያዬ ሰው፣ያለሰውም ምንም የማይሆንልኝ ሰው ነኝ ወደሚል ያዘነብላል፡ ይህ ደግሞ ይዘቱን ያሳሳዋል፡፡
***
ሁለት፤- የሕይወቴ ፈርጦች የተባለለት ርዕሰ ነገር የገለፃቸውን ፈርጦች በበለጠ ሊሻገር በሚችል ቤተሰብ፣ሀገር፣ክርስትያን ማህበረሰብን እና በሰፊ አድማሱ ዓለምን ሊለውጥ እና ሊጠቅም የሚችልን መልክእት ግለ ታሪኩ ቢያካትት ትረካው እና ርዕሱ የተጣጣሙ ይሆኑ ነበር፡፡ ‹‹እኔም ፈለጉን ልከተል..›› በሚያሰኝ መልክእት ቢዳብር የተሸለ ውጤት ማምጣት ይቻላል፡፡
***
ሦስት፤-ክርስትና ከክርስቶስ የውጀት ሥራ እና ከትምህርቱ እውነትነት የተነሳ ለዚህች ዓለም ሁነኛ መፍትሔ ሆኖ ያለፉትን ሁለት ሺህ አመታት ለብዙዎች በረከት ሆኑዋል፡፡ ክርሰትና መሰረታዊ ትምህርቶች አሉት /አይቀሬ እና አይዘንጌ አስተምህሮዎች/፡፡ እነዚህ ደግሞ በስድሳ ስድስቱ ቅዱሳት መፅሐፍት ውስጥ ሰፍረዋል፤በእነርሱ መመራት የማያመቻምቹበት ተግባር ነው፤፤ቃሉ ባለው መፅናት ያንንም ማስተዋወቅ፣ተገቢ ነው፡፡በዚህ ግለ ታሪክ አልፎ አልፎ ይህን ሁነኛ ጭብጥ የአለማስተናገድ ክፍተት ታይቱዋል፡፡ለምሳሌ ‹‹በሕይወቴ የመጣው ብርሀን ታላቅ ነው… ያ በርሀን ከስጋት ነፃ አድርጎኛል…›› (ገፅ 10) የሚለውን በምሳሌነት ቢነሳ ደራሲው ‹‹የሚገባው ይገባዋል›› ከሚል ቅን ፍላጎት በመነሳት
ያስነበበን ካልሆነ በቀር መልዕክቱ ድፍን ነው፡፡እርግጥፀሐፊው ፍንጭ የሰጠበት ብርሀን ሐጢያትን ይገልፃል፣መስቀሉን ያመላክታል፡መንፈስ ቅዱስ ወቃሽም አፅናኝም ሆኖ ከማምለጫው ጋር ያገናኛል፡፡ንስሀ መግባት እና ዳግም መወለድ ተአምራዊ ውጤቶች ሆነው ሲከታተሉ የሚያሳይም ይሆናል ይህ ግን ከመፅሐፉ አልተገኝም፡፡
***
በተያያዥ ቤተሰብን አስመልክቶ የተተወውን ክፍተት ገልጬ ልጨርስ፤- የግለ ታሪኩ ፀሐፊ ዘመደ ብዙ ላይሆን ይችላል፡፡ግና እናት አለው፤ፍቅርተ ታደሰ የምትባል ሚስትም ኖሮት ‹‹ልጆቼ›› የሚላቸውን ርብቃንና ኤፍሬምን መውለዱን በገፅ 262 ላይ አስተዋውቆናል፡፡ ወደ ፍቅርተ ለመድረስ የእነደጅጥኑ፣የእነፈትለ ታሪክ ተነስቶ ባለበት የታሪክ ሂደት ውስጥ ፀሐፊው ከእርሱ እና ከበላቤቱ መቀናጀት (መጣመር)የተነሳ የሆነውን ምንም አልነገረንም፡፡በተያያዥ ስለ ወይዘሮ የሺ ዓሊም በገፅ 252 ላይ የምስጋና ቃል እንዲሁም በገፅ 262 ዳግም ከማመስገን ውጭ ደራሲው እናትነትን አስመልክቶ እንድንጨብጥ ያደረገን ነገር ትንሽ ነው፡፡እነዚህ ከግለ ታሪክ ተጠብቀው የታጡ ናቸው፡፡
***
ፀሐፊው በቀጥታ የማይመለከት ግን በመፅሐፉ የውስጥ ገፅ ላይ ውበቱን ያደበዘዘ ሥራ ርዕሶቹን ከግርጌ አጉል ቦታ ላይ ማኖር ነው፡፡ይህን በገፅ 83፣86፣99፣148፣164…ላይ መመልከት ይቻላል፡፡ይህም በቀጣዩ ሥራው ትኩረት ይሰጠዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡
***
እንኪያስ ‹‹የሕይወቴ ፈርጦች›› ትልቁ ሀብታችን ነው፡፡የንባብ ባህልን ከማዳበር አኩዋያ እንዲሁም ምስክርነትን በቅጡ ‹‹እኔ››ብሎ ከመናገር እና ከግለ ታሪክ የአቀራረብ ዘዴ አኩያ በርካታ ጥቅሞችን አግኝተናል፡፡ከዚህ ደግሞ በመነሳት ባልታዩ ርዕሰ ነገሮች ላይ ጥናት ለማድረግ ለሚነሳሳ የትኛውም ኢትዮጵያዊ ይህ መፅሐፍ በብዙ ጠቕሙዋል የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፡፡የሌላቹ ይኑራቹሁ፤ያለቹ ደግሞ በእኔስ ታሪክ እግዚአብሔር ምን አየሰራ ነው በማለት ለመፀፍ ተነሳሱ፡፡አበቃሁ፡፡ ልዑል እግዚአብሔር ዓለማየሁ ማሞን እና ቤተሰቡን እኛንም ጭምር ይባርክ፡፡ አሜን፡
Like
Comment