Monday, December 29, 2014

ዓመቱ በጥቂት ቃላት

ዓመቱ በጥቂት ቃላት
ይህ ዓመት በርግጥም ስኬታማ ነበር። ዓመታት የሚፈጁ ክንውኖችን በአስራሁለቱ ወራት ውስጥ እንዳካሂድ እግዚአብሔር በምትታይ እጅ ረድቶኛል።
ከነሐሴ አስራአምስት ጀምሮ ለሦስት ቀናት በሚኒሦታ ክፍለ ግዛት መንትዮቹ ከተሞች (ሴንት ፖል እና ሚኒያፖሊስ) የነበረኝ አገልግሎት አቅጣጫ ቀያሪ ነበር። ለሥራ መፈታቴን አመላክቷልና። ከአንጋፋው ሰባኬ ወንጌል ቄስ በልዕና ሣርካ ጋር ያገጣጠመኝ ይኸው የወንጌል ስርጭት ኮንፍራንስ በብዙ መልኩ ፍሬያማ ነበር። እግረ መንገዴንም ከሁሉም ይገዝፋል የሚባለውን “ሞል ኦፍ አሜሪካ” በከፊል መጎብኘት ችያለሁ።
ክፍል አንድ የሕይወት ታሪኬን ሳሳትም ብሎም ነሐሴ 7 ቀን 2013 (..) ሳስመርቅ ጉዳዩ የሦስቱ ክፍለ ግዛቶች ማለትም ዲስትሪክት ኦቭ ኮሎምቢያ፣ ሜሪላንድና ቨርጂኒያ አበሾች መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። መቼም በአገራችን ታሪክ አምሳ ዓመት ያልሞላው ሰው ደፍሮ ታሪኩን ሲጽፈው አልታየም። ለነገሩ አንድ አንባቢ እንዳለኝ እንኳን ሊጽፈው ገና መቼ መኖር ጀመረና?
በአስራ አንድ ወሩ ደግሞ እነሆ በንጉሡ ጸጋ ሌላ ሪኮርድ በርኩ። ሐምሌ አንድ ላይ የሦስትዮሽ መጻሕፍት ምረቃ ማካሄዴ የዓመቱ ታላቅ ክንውን ነው ማለት ይቻላል። በዚሁ ፕሮግራም ላይ ከተናገርኩት ውስጥ “በአገራችን የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ከአንድ ጸሐፊ ጓዳ ሦስት መጻሕፍት በአንድ ጊዜ ተዘጋጅተው፣ ታትመውና ተመርቀው አያውቁም። ይህ ዓይነቱ ክንውን አልታየም፤ አልተሰማም። ስለዚህ ይህ ዝግጅት በየተኛውም መለኪያ ጥቂቶች የታደሙበት ታላቅ ድግስ ነው” የሚል ይገኝበታል። ይህ ሁሉን ስለሚገልጠው ተጨማሪ ሐተታ አያሻም።
በርካታ ወዳጆቼና የሙያ ባልደረቦቼ ይልቁንም ተጋባዥ እንግዶች በሥርዓቱ ላይ ቢገኙም ከቦስተን ድረስ በመምጣት ሪኮርዱን የሰበረው ግን የመቶ አለቃ በላይነህ ዲንሣሞ ነው። ለነገሩ እርሱ ሪኮርድ መስበር ዱሮም ያውቅበታል። ሰው ቢረሳ ሮተርዳም ይህንን አትረሳም። ልጆቼ ርብቃና ኤፍሬምም ሬኮርደርና ክላርኔት በመጫወት ዝግጅቱን ውበት ጨምረውለታል።
 ሐምሌ መጨረሻ ላይ ለሁለት ቀናት ወደንግሥቲቱ ከተማ (ሻርለት) ተሻግሬ ማገልገሌና መገልገሌ ሌላው ስኬት ነው። በአንድ ቀን ምሽት አዲስ ሕይወት ቤ/ክ ውስጥ መስበክ ስጨርስ ደግሞ ወደሌላ ክንፍራንስ ተወስጄ ስለመጽሐፎቼ መናገር ችያለሁ። በሚቀጥለው ቀን ደግሞ ጧት ከጸሓፍት ጋር ተወያይቼ ከሰዓት በኋላ ደግሞ የቢሊ ግራሃምን ቤተ መጻሕፍት ጎብኝቼ ሳበቃ ማምሻውን በርሬ ወደምኖርበት አስፐን ሒል መመለስ ችያለሁ።
ከሚኒሦታ እንደተመለስኩ ስፕሪንግፊልድ ላይ በተካሄደ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ከቤሪያ አስተባባሪዎች ጋር ጠንካራ ወዳጅነት ለመመስረት በቅቻለሁ። ያም በአራት ወራት ውስጥ አፍርቶ በስልክ መስመራቸው ላይ ተከታታይ ትምህርት ለማቅረብ በሩ ይከፈትልኝ ዘንድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። በዚሁም መሠረት ከጥቅምት ሃያ አንድ ጀምሮ ለስምንት ተከታታይ ሳምንታት ያህል “ጥበብን ፍለጋ” በሚል ርዕስ በመቶዎች ለሚቆጠሩት ታዳሚዎች ጠቃሚ አሳቦችን በብዙ ደስታ አካፍያለሁ።  ምናልባትም በአዲሱ ዓመት እልባት እናበጅለት ይሆናል። (ሻርለት ደርሼ የመጣሁትም በመሃሉ ነው።)
በነዚህ ሁሉ የረዳኝን ጌታ አመሰግናለሁ። ሁሉ ነገር ግን የጫጉላ ሽርሽር ነበር ማለት አይደለም። በተለይ በጤና ረገድ ጥቂት ውጣ ውረዶች ነበሩብኝ። ከሁሉ የከበደው ግን በዚሁ ባሳለፍነው ሳምንት መኪናዬን እየነዳሁ ሄጄ ከሠላሳ ስድስት ዓመታት በኋላ ሆስፒታል መተኛቴና ከአስር ዓመት በኋላ ፀረ ተኅዋስ መድኃኒት መውሰዴ በሦስተኛው ቀን ደግሞ  “ገናን ከቤተሰብህ ጋር ለማክበር ብቁ ነህ” ተብዬ መሰናበቴ ነው።
በመጨረሻም እነዚህ ሁሉ ሰፋ ባለ መልኩ በማሳታወሻዬ ስለሰፈሩ ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም ወደፊት አንድ መድብል ሊወጣቸው ይችላል።    

ድንቅ ዓመት !

Saturday, December 20, 2014

ምስጋና

ወንድሜ ሆይ ለማመስገን የግድ ከክፍልህ አንደኛ መውጣት አያስፈልግህም። ዓመቱን ሙሉ ተመላልሰህ በሰላም ለመማር መብቃትህ ራሱ ከበቂ በላይ ምክንያት ነው። ለማመስገን ሮጠህ በአንደኝነት መሸለም አያሻህም። ዝለህ ሳትወድቅ ውድድሩን መጨረስህ ወይም በተመልካችነት መታደምህ ራሱ የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ታላቅ ዕድል ነው። 
ለማመስገን ምርጥና ዘመናዊ መኪና እስክትነዳ መጠበቅ ሞኝ ያስብልሃል። በማይሌጅ የበለጠገችው ኩርኩር መኪናህ ቀለበት መንገድ ላይ ሳትገትርህ ጎታች መኪና ጥበቃ ብርድና ሐሩር ላይ ሳታቆምህ በደህና ቤትህ መግባትህ የሎተሪ ያህል አስደሳች ዕጣ ነው።

ለማመስገን ከተጠናወተህ ደዌ እስክትፈወስ መጠበቅ አይተው ከሚያምኑት ተጠራጣሪዎች ጎራ ያቆምሃል። ግን ቆመህ መሄድህ ራሱ ተአምር እንደሆነ አምነህ ብታመሰግን ያምርብሃል።

Friday, December 19, 2014

አሜን እንበል

የሰባኪዎች ልዑል ተብሎ የሚጠራውን ቻርልስ ስፐርጅንን ማስተዋወቅ አያሻኝም። የዚህ ሰው ጸሎት ከስብከት ያልተናነሰ በመሆኑ ብዙዎች አብረውት ከመጸለይ ይልቅ የሚለውን በማስታወሻቸው ለመጻፍ ይፍጨረጨሩ ነበር። ያንን ለማርገብ ሲባል በአንድ ምሽት አገልግሎት መክፈቻ ላይ ያቀረበው ጸሎት ተመዝግቦ ለመዘክርነት ተቀመጠ። እንዲህ ነበር።
“ጌታ ሆይ እባክህ ሕዝብህን አድን፤ ሕዝብህን አድን። ጸሎቴ በፊትህ መሆን እንደሚገባው እንዳልሆነ አምናለሁ። በጸጋህ እርዳኝ። በሰጠኸኝ ዕድሜና ኃይል እንደሚገባ እንዳልሰበክሁ ግልጽ ነው። ጌታ ሆይ በእኔ በደል ሌሎችን ቸል አትበል። ሕዝብህን አድን። በእረኛው ጥፋት መንጋውን አትምታ። ይቅር በላቸው አባት ሆይ፤ ምሕረትህ ከእነርሱ ጋር ትሁን።
ይቅርታን ያላገኙ ብዙዎች በዚህ አሉ። ይድኑ ዘንድ ምን ያህል እንደደከምን አንተ ታውቃለህና አልዋሽም። የሰው ልብ ጠንካራ ነው አባት ሆይ፤ ነፍሱም እንደ ብረት ነች። ደምና ሥጋ ሰውን ሊለውጥ አይችልም። መጋቢው ተስፋ ያደርጋል፤ አገልጋይህም ያምናል። ግን ሁለቱም ማዳን አይሆንላቸውም። ጌታ ሆይ አንተ ግን በኃይልህ ትችላለህ። አንተ ካልሳብካቸው ሊከተሉህ አይችሉም።
የእሥራኤል አምላክ ሆይ በዚህ ዓመት ደግሞ ይህችን ቤተ ክርስቲያን እርዳ። ሕዝብህን በጸሎት ባርክ። ሥጋን በመንፈስ ይገድሉ ዘንድ አበርታቸው። በዚህ ብቻ ሳይሆን በሁሉ ሥፍራ ኢየሩሳሌምን ለምስጋና እስክታደርጋት ድረስ አንዳያርፉ እርዳቸው። ጸሎትን ጨምር ጌታ ሆይ።
የምንጮኸውና የምናነባው ስለ ቤተ ክርስቲያንህ ብቻ አይደለም። ስለ ዓለም ሁሉ እንጂ። በከንቱ እንደማልደክም አልተናገርኸኝምን? ለባሪያዎችህስ ይህንኑ አላልክምን? እንግዲያውስ በሰዎች መዳን አጥግበን። “ዝናብና በረዶ ከሰማይ እንደሚወርድ ምድርን እንደሚያረካት ታበቅልና ታፈራም ዘንድ እንደሚያደርጋት ዘርንም ለሚዘራ እንጀራንም ለሚበላ እንደሚሰጥ እንጂ ወደ ሰማይ እንደማይመለስ ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ይሆናል” ተብሎ እንደተጻፈ ቤተ ክርስቲያንህን አስፋ። አስፋልን ጌታ ሆይ።
ዛሬም በዚህ ምሽት ቃልህ በከንቱ አይመለስ። ባሪያህ በቅን ልብ በፍቅርና በርኅራኄ እንዲሰብክ እርዳው። መንፈስ ቅዱስ ሆይ ና! ያላንተ ምንም ልናደርግ አንችልምና በትኅትና እንጋብዝሃለን። በአብርሐም፤ ይስሐቅና ያዕቆብ ላይ የነበርክ የከበሩ ሕልሞችን ለሰዎች ትንቢትን ለነቢያት የሰጠህ በሐዋርያትና በቀደመችው ቤተ ክርስቲያን ላይ ያደርክ ታላቁ የእግዚአብሔር መንፈስ ሆይ በዚህች ምሽት ከእኛ ጋር ሁን። ይህች ምድር ትናወጥ። ነፍሳትም ልባቸውን ከፍተው የከበረውን ቃል ይስሙ። ሥጋ ለባሽ ሁሉ አንተን በማወደስ ሐሤት ያድርግ። ለዘላለም ለሚኖረውና ከፍ ላለው ለአብ፤ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ክብር ይሁን፤ አሜን!”
እኛም አሜን እንበል.....



Thursday, December 18, 2014

እንዲህ ነው ለካ?

በምትሠራው ሥራ በአነጋገርህ፣
አንዲት ምዕራፍ ወንጌል በቀን መጻፍህ፣
እንጋይዘነጋህ እንዳይረሳህ።
ሰዎች ያነቡታል ያን የጻፍከውን፣
የእምነት ጽናትህን ለእውነት መቆምህን፣
አዳኙን ያሳይ ዘንድ የጠራ ይሁን።

          ከምንጩ ልጀምር። አንድ ያልታወቀ ሰው ቋጥሮት ወዳጄ ግርማዊ በመጽሓፍ ውስጥ ተሸንቅሮ አገኘውና ወደ አማርኛ መለሰው። እኔ አቃናሁት። ይህ ከሆነ ከዓመታት በኋላ ተመልሼ ሳየው ገጣሚው እንዲህ ሲለን አገኘሁት። ጽሑፉ የሚጀመረው ከአኗኗራችን ነው። በጥቂት መስመሮች እንደሚለን አነጋገርም ሆነ ሥራችን በየቀኑ ይናገራል። ሰዎችም ያዩታል፤ ያነቡታል። ያልኖርነውን ብንናገር ወይም ያልተናገርነውን ብንኖር ምን ፋይዳ አለው?    


Tuesday, December 16, 2014

ተደርቦና ተደራርቦ

ተደርቦና ተደራርቦ

ማዕበል የተለመደ የውኃ ላይ ነውጥ ቢሆንም አደገኛ የሚሆነው በተደራራቢነቱ ነው። እያንዳንድዋ የውሃ ጉማጅ ትጋፋለች። በአንዱ ተንገዳግዶ መቆም ሲቻል አንዱ ባንዱ ላይ እየተነባበረ ሲመጣ ግን ከአቅም በላይ ይሆናል። እንዲሁም ችግር የሕይወት ጥላ ቢሆንም የበለጠ አስቸጋሪ የሚሆነው ተደርቦና ተደራርቦ ሲመጣ ነው። ሁለቱን አስማሚ ፍች ከሠጠናቸው በኋላ ጥቂት ማብራሪያ ማከል ይኖርብናል። ተደርቦ ስንል ከዚያ ቀደም ብሎ የተከሰተው ችግር ከመፈታቱ በፊት ሌላው የመድረሱን እውነታ ተከትለን ነው። ተደራርቦ ካልን ደግሞ ከመደረብም አልፎ በላይ በላዩ ተቆልሏል ማለት ነው። በአገራችን መደረብ ወይም መደራረብን ጥሩ አድርገው የሚገልጡ አባባሎች አሉን። የመጀመሪያው በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሚለው ነው። በቡሃ ላይ ቆረቆር ሊባልም ይችላል። በድንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ ወይም ከአባ ቁፍር እሸት ተበልቶለት እሚሉትም ቢሆኑ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው።