መንፈሳዊና ለትርፍ ያልተቋቋሙ የበጎ አድራጎትድርጅቶች እንዲሁም የተለያዩ አገልግሎቶች ከቀረጥ ነፃ የሚሆኑበት አሠራር በምዕራቡ
ዓለም የተለመደ ነው። ይሄ ለብዙዎች ማበረታቻ ሆኗል። ለምን ቢሉ
የሚያገኙትን ገንዘብ ያለምንም ገደብ ለወንጌልና የበጎ አድራጎት አገልግሎት
ሊጠቀሙ ይችላሉ። ለጋሾችም ለነዚህ ድርጅቶች የሚሰጡት የገንዘብም ሆነ የንብረት ስጦታ ከቀረጥ ነፃ ስለሚሆንላቸው የበለጠ ለመስጠት
ይበረታታሉ። ነገር ግን እነዚህን መንፈሳዊና ለትርፍ ያልተቋቋሙ የበጎ አድራጎትድርጅቶች እንዲሁም የተለያዩ አገልግሎቶችን ከማዕበል ነፃ የሚያደርግ አሠራር የለም።
ስለዚህ የአዳም ዘር ሁሉ ራሱን ለማዕበል ማዘጋጀት ይኖርበታል።
የሚገርመው ደግሞ ልክ ምድራዊው ነውጥ ማለትም የመሬት መንቀጥቀጥ፤ ዐውሎ ነፋስና የባሕር ማዕበል
አማኝና ከሃዲን ሳይለይ የሰውን ዘር በሙሉ እንደሚመታ ሁሉ ውስጣዊው ነውጥም እንደዚያው ነው። በማያምኑት ላይ ያየናቸውን ብሎም
የተሳቀቅንባቸውን በሽታዎች በወገኖችም ላይ ልናያቸው እንችላለን። በአገር ላይ የሚመጣው ማንኛውም ችግር ዜጎችን ሁሉ ይመለከታል።
ኢኮኖሚውን ተከትሎ የሚከሰተው የኑሮ ውድነት ወይም የዋጋ ግሽበት ለአማኞችም ይተርፋል። ቤተ ክርስቲያን ይህን ለመቋቋም የከፈተችው
የሕብረት ሱቅ የለም። እንሻገራለን ቢባል እንኳ ብዙውን ጊዜ መሻገር የሚሆነው መጀመሪያው ችግሩ ከተቀመሰ በኋላ ነው።
እናም ዛሬ በሕይወት ያለን ሁላችን ከሁለት አንዱ ውስጥ እንመደባለን። የማዕበል መንገደኞች
ወይም ሰላማዊ ቀዛፊዎች ነን። ወይ ማዕበሉ ውስጥ ገብተናል አልያም ወደ ማዕበሉ እየተጠጋን ነው። በወጀቡ ውስጥ አረፋ የሚደፍቁትን
እያየ ለመቆዘም ወይም ለመሳቅ የተመደበ የሰው ዘር የለም። እንደምንኖርበት መልክዓ ምድርና እንደ እምነታችንም መጠን የማዕበሉ ኃይል
ሊለያይ ቢችልም እውነቱ ግን እንደጥላ የትም ይከተለናል። እናም ሐቁ ይህ ነው። ወይ ማዕበሉ ውስጥ ገብተናል አልያም ወደማዕበሉ
እየተጠጋን ነው። መልካም ቀዘፋ!
የማዕበል መንገደኞች ከተሰኘው መጽሓፌ የተወሰደ
No comments:
Post a Comment