Thursday, July 18, 2013

ስማችንን ያስጠሩ

 
እነሆ በሁለት ሠፈርተኞች ወግ እንጀምር። ታላቁ የመንግሥት ሠራተኛ ነበር። ከደመወዙ ሌላ
የሚያገኘው አበልና ጥቅማጥቅም ብቻ ሁለተኛ ቤተሰብ ሊያስተዳድር ይችል ነበር ተብሎ ይታማል። ግን
ምን ያደርጋል “አብሮ መብላቱና መጠጣት ባልነበር፤ የእንቶኔ ገንዘብ ፎቅ ይሠራ ነበር” ክሚለው የአዝማሪ
ግጥም አልዘለለም። እሱ ግን ከዚያም ያለፈ ቅሬታ ነበረውና አጋጣሚውን ተጠቅሞ ወደአሜሪካ እብስ
ይላል። በገንዘብ ረገድ ከተስፋይቱ ምድር ይልቅ አገር ቤት የተሻለ ጡንቻ
እንደነበረው ለመገንዘብ ግን ጊዜ አልወሰደበትም። እናም ከአለፍ አገደም መቶና ሁለት መቶ ዶላር ለእናቱ
ከመወርወር ያለፈ ምንም ሊያደርግ አልቻለም። አንድ አሥርት ዓመት እንዲያ ነጎደ።
ታናሹ የሠፈሩ ልጅ ደግሞ ዲቪ እሚባለው ዕጣ ወጥቶለት ወይም ወጥቶበት በዘመነኛው ቦይንግ
አቆራርጦ ዋሽንግተን ዲ ሲ ዱብ ይላል። እንደዚያኛው ወረቀቱን እስኪያገኝ እንኳ መቅለስለስ ሳያስፈልገው
ሥራ ያገኛል። ለእናቱና አባቱ ለእህቶቹና ወንድሞቹ ብቻ አይደለም ዶላር መበጠስ የጀመረው። አብሮ
አደጎቹን የቅርብ ጓደኞቹን ጎረቤቶቹንና ሌሎችንም የአሜሪካን ብር ረጨባቸው። ይባስ ብሎ በሁለተኛ
ዓመቱ ለጉብኝት ወደሸገር ተሻገረና ታላላቅ ጀብዶችን ፈጸመ። የመጀመሪያው ለእናቱ የተንጣለለ ቪላ
መግዛቱ ነው። መጀመሪያውንም የሠፈሩ ጭቃ አንገፍግፎአቸው የነበሩት እኒያ እናት አቧራውንም
ተሰናብተው ወደዘመናዊ መንደር ዘለቁ። ድኅነትንማ ባለፉት ሁለት ዓመታት በዶላር መዶሻ አናቱን
መምታት ችለዋል። ታናሽ እህቱ የራሷን የጸጉር ቤት ሥራ እንድትጀምር ወንድሙ ደግሞ የግሉን ታክሲ
እንዲያሽከረክር ለማድረግ ሁለት ሣምንት አልፈጀበትም። ሰላምታ ሊሰጡ የመጡ ሁሉ እጃቸው
የተጨበጠው በድፍን መቶ ብር ነበርና የመንደሩ ሰበር ዜና የእርሱ ለጉብኝት መምጣት ሆነ። እንግዲህ
ማለቅ አይቀርምና ለሁለት ዓመት የከሰባትን በትኖ ለሌላ ሽቀላ በቦሌ ሲሰናበት የመንደሩ ወሬ ተቀየረ።
ተረስቶ የነበረውና አሜሪካ ከገባ 10 ዓመት ያስቆጠረው የእትዬ እከሊት ልጅ ነገር ተነሳ። የቡና ማጣጫም
ሆነ። እናቱ እሁንም በቀበሌ ቤት ነው የሚኖሩት። ጉብኝት እምትባል አስቦ አያውቅም። እናም ስሙ በክፉ
ተነሳ። ከዚያ ሳተና
መቶ መቶ ብር የተቀበሉትና ለእናቱም ቤት ምርቃት ግብር የበሉት የመንደሩ ሰዎች ይህኛውን ረገሙት።
ራስ ወዳድ፤ ሆዳም፤ ሕሊና ቢስ አሉት። ለመሆኑ የነዚህ ሁለት መንደርተኞች ታሪክ ለየቅል የመሆኑ
ምሥጢር ምንድነው? አዎን ምሥጢሩ የሚሠሩት ሥራ ነው። ታላቁ ይሠራል። የሚበቃውን ያገኛል።
ታናሹ ግን የሚያበላ ሥራ ነው እሚሠራው። እሚያበላ ሥራስ ምንድነው? እሚያበላ ሥራማ ደሞዝ
መጠበቅ ሳያስፈልግ ዶላር እንደቡና ቁርስ እሚዘገንበት ነው። የሳምንቱ ክፍያ በአንድ ቀን ውስጥ
እሚመነተፍበት ነው። አስረጂዎች እነሆ!
በቅርቡ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ቀዳሚ መወያያ ከሆኑት መሃል ፍርድ ቤት የቀረቡት ሁለት የኛ ሰዎች
ናቸው። እናም ገና በተጀመረው አዲሱ የአውሮፓውያን ዓመት መባቻ ስማችንን አስጠርተዋል። በመኪናዬ
ሬዲዮ መሠረት የሚል ስም ሲጠራ ልማደኛዋ መሢ ቦስተን መጥታ ያሸነፈች መስሎኝ ነበር። ለካስ
ጨዋታው የእንብላው ሩጫ ኖሮአል። በቀጥታ ወደጉዳዩ እንዝለቅ።
ነዋሪነቱን በሲልቨር ስፕሪንግ ያደረገው የ37 ዓመቱ መሠረት ተረፈ በአሌክሳንደሪያ ፌዴራል ፍርድ ቤት
ቀርቦ የአንድ ዓመት ከስምንት ወር እስራት የተፈረደበት ሲሆን ሳያስፈቅድ የወሰደውንም $487,000
እንዲመልስ ተነግሮታል። በሰሜን ቨርጂኒያ ብሔራዊ የአየርና ሕዋው ሙዚየም በሠራባቸው ሦስት
ዓመታት ማታ ማታ ብሩን በእጅ ሻንጣ እያጨቀ ወደመኪናው የኋላ ኮፈን ይከት የነበረው ተሬ
$218,000 ያህሉ በአፓርትመንቱ ውስጥ እንደቆለፈበት ተገኝቶአል። ቀሪውን ገንዘብ አ/አ ውስጥ
ኮንዶሚኒየም እንደገዛበት ታውቋል።
በቀን እስከ $4,000 በመመንተፍ ካስተናገደቻቸው 59,712 የሚገመቱ መኪኖች የተገኘውን ገቢ አንድ
ሦስተኛውን ለራሷ አስቀርታለች የተባለችው የ46 ዓመቷ ፍሬወይኒ መብራህቱ ደግሞ $900,000 ዶላር
መስረቋን አምናለች።. የ27 ወራት እስራት ነው የተፈረደባት.ሲሆን ስትለቀቅም ለሌላ ሦስት ዓመታት
በዐይነ ቁራኛ እንድትጠበቅ ተብሎአል። በተጨማሪም $895,680 እንድትከፍል ታዛለች።
“ገንዘቡን ለልጆቿ የኮሌጅ ክፍያ ለሴት ልጅዋ የቀዶ ሕክምና ወጪ አውላዋለች። ወደአገር ቤት
መድኃኒትና ልብሶችን ልካበታለች። ለመስጊዶችም ስጦታ አበርክታለች” ይላል የፌዴራሉ ምርመራ
ቢሮ(ኤፍ.ቢ.አይ)ዘገባ። አርቆ አሳቢዋ ፍሬወይኒ በራሷ ብቻ አልተወሰነችም። ሌሎች ባልደረቦቿንም
እንዴት መመንተፍ እንደሚቻል አስተምራቸዋለች። እነርሱ በቅንነት ከሠሩ የገንዘቡ ልዩነት ሊታስነቃ
ይችላልና።
ለመሆኑ እንዴት ተደረሰባቸው? በጥቆማ ነው። ከዚያም ከሙዚየሙና ከኤፍ.ቢ.አይ የተውጣጡ
ባለሙያዎች ወጪ ገቢዎቹን መኪኖች እየቆጠሩ ከማታው ሪፖርት ጋር ማመሳከር ጀመሩ።
የሙዚየሞቹ ቃል አቀባይ የሆኑት ክሌይር ብራውን በበኩላቸው “የሚያቀርቡት ዘገባና ገቢው ተመሳሳይ
በመሆኑ ዝርፊያ ይኖራል የሚል ጥርጣሬ አልነበረንም” ይላሉ። ባለፉት ሦስት ዓመታት ጋራዡ ሊያገኝ
ከሚገባው ገንዘብ አስር ከመቶው ሁለቱ ወገኖቻችን ኪስ ወድቋል እንደዐዋቂዎቹ ስሌት። ምን ያህል
መኪኖች እንደገቡ የሚያሳየውን ማሽን በመንቀልና የየቀኑንም ዘገባ በመሸቀብ ከ2009 ጀምሮ $1.4
ሚሊዮን ዶላር ከድርጅቱ ተዘርፎአል።.
ሌላዋና ሦስተኛዋ ተጠርጣሪ $120,000 ወስዳለች በሚል ጉዳይዋ በፍርድ ቤት ሊታይ ቢቀጠርም
ቀድማ ራሷን በመግደልዋ ፋይሉ ተዘግቷል። የፍርድ ቤቱ ሪፖርት ስሟን ያላነሳ ቢሆንም ናዝሬት በተሰኘ
ድረ ገጽ ላይ ስሟ ገነት እንደሚባል አንብቤያለሁ። እንግዲህ እስዋም የኛው ሰው ነበረች ማለት ነው።
እኒህ ሦስት ግለሰቦች እንግዲህ የድርጅቱን ቴክኖሎጂ ለማሳደግ አስተዋፅዖ አድርገዋል ካልተባለ በቀር
በምንም መንገድ የሚመሰገኑበት ቀዳዳ የለም። ግን ድርጅቱ እዲስ ዓይነት የቁጥጥር ማሽን ዘርግቶአልና
በዚያ ሊታወሱ ይችላሉ። ለማንኛውም እንዲያ እንዲያ እያሉ የአገራችን ቁጭበሉዎች የአሜሪካን ኢኮኖሚ
ብቻ ሳይሆን የማኅበረሰባችንንም ስም እየቦጠቦጡ ነው።
አንድ ተማሪ ወደኮሌጅ ሊገባ ያመለክትና ርዕሦችን መርጦ ጽሑፍ እንዲያቀርብ ይጠየቃል። እናም
ስለእግዚአብሔር እና ስለሰይጣን የሚያውቀውን አንድ አንድ ገጽ እንዲጽፍ ይነገረውና ይጀምራል።
በተለይ ስለእግዚአብሔር መልካምነት የሚችለውን ሁሉ ባማሩ ቃላት ሲከሽን ይቆይና ሰዓቱ ያልቅበታል።
ይህን ጊዜ ስለሰይጣን እንዲጽፍ በተሰጠው ሥፍራ ላይ አንዲት ዐረፍተ ነገር በጥድፊያ ጭሮ መለሰ አሉ።፡
”ስለሰይጣን ለመጻፍ ጊዜ የለኝም!”
እኔም ይህችን የጫርኩት በተመሳሳይ ስሜት ውስጥ ሆኜ ነው። ከእኛው መሃል በበጎ ምግባርም ይሁን
በልቀት የሚመሰገኑ ሲኖሩ ስለነርሱ ብጽፍ ደስ ይለኛል። ስለሌቦች ለመጻፍ ግን ከዚህ በላይ ጊዜ የለኝም።

No comments:

Post a Comment