ከልጅነቴ ጀምሮ ልጆችን እወዳለሁ። ለአቅመ አዳም ከደረስኩም በኋላ ቢሆን ጓደኞቼና አጃቢዎቼ ልጆች ነበሩ። ታላቁ ብርሃን
ከበራልኝ በኋላ ደግሞ ያ ፍቅር በእጅጉ ጨመረ። ዋኘኛ ምክንያቱ ይህ ይመስለኛል። ያዳነኝ ጌታ ልጆችን እጅግ ይወዳል። በአገልግሎቱ
ዘመን ወረፋ ሳይጠብቁ ወደርሱ እንዲቀርቡ ፈቅዶላቸው ነበር። ያንንም ፍቃድ “አትከልክሏቸው” ሲል አትሞበታል።
ከማግባቴ በፊት እና በፈጣኑ የሩጫ ዘመን እርሱም 1993 ዓ.ም እንደአገራችን አቆጣጠር ስለልጆች
የምታወሳ አንዲት ባለ ሰማንያ ገጽ መጽሐፍ አሳትሜ ነበር። የዛሬን ያድርገውና በእስክርቢቶና ወረቀት በምጽፍበት በዚያ ዓመት ያች
እትም እንደትልቅ መቆጠሯ አልቀረም። ጠቅማናለች ያሉ ሰዎችም ጽፈውልኛል። ስለሆነው ሁሉ ክብር ለአባታችን ይሁን! አሁን ዓመታትን
ቆጥሬ ከወለድኩና ከከበድኩ በኋላ አንሥቼ ሳነባት በማነሧ ራሴን ወቀስኩ። በዚያ ላይ “በርግጥም በወላጆች ላይ ከብጄባቸው ነበር”
ብዬ ተጸጸትኩ። ከሩቅ ሆኖ እንዲህ ነው ማለትና ገብቶ መጫወት ለየቅል እንደሆኑ ተብራርቶ ገባኝ። እንዲያ ሆኖ ለተጨማሪ ዓመታት
ዝም ብዬ አደፈጥኩ። ብዙ ብልም ስለቤተሰብ ጽፌ አላውቅም።
አሁን ግን ጊዜው ደረሰ።
ወደዚሁ ወሳኝ ርዕስ እንዲህና እንዲያ አድርጉ የሚለውን ወደጎን ጥዬ እንዲህና እንዲያ እናድርግ
እያልኩ ተመልሻለሁ። ስለልጆች ሁሉን ያካተተ መጽሐፍ ይዤላችሁ መጣሁ ግን አላልኩም። ከዘመናቸን ፈጣን ግሥጋሤ ጋር እየተቀላቀለ
ማለቂያ የሌለው ርዕስ ሆኗልና። በአጠገቤ ያለፉትን ወሳኝ ነጥቦች ግን በሚገባ አበጥሬአቸዋለሁ!
እናም ይህኛው ካለፈው ዳጎስ ያለ መጽሐፍ ለወላጆች፣ ለመምህራን እና አገልጋዮች ጥሩ ማገናዘቢያ
ይሆናል ብዬ አስባለሁ። ከግቢም አልፎ እንደእኔ ለማያምኑ ሰዎች ሊጠቅም ይችላል ባይ ነኝ።
አሁንም ይህንን ሳቀርብ በሁሉ የነጠርኩ፣ የምለውንም ጨርሼ በሥራ የተገበርኩና የበቃሁ ተደርጌ
እንዳልቆጠር አደራዬ የተገለጠ ነው። እኔም እንደናንተው ብርሃን ለማኝ ነኝ። ቤተሰቤን መርቼ እንጂ እንጀራ ብቻ በልቼ እንዳልሞት
የሠርክ ጸሎቴ ነው። ጭንቃችሁ ጭንቄ ከሆነ ዓመታት ተቆጠሩ። ማቀርቀሬ ያየሁትን፣ ያነበብኩትንና ይልቁንም ከቃሉ የቀሰምኩትን ላካፍል
ነው ። የመጻፍ ተሰጥዖዬን በወረቀት ላይ ላቃምስ እንጂ በማንም ልፈርድ እንዳልመጣሁ ተረዱና ወደንባቡ ዝለቁ።
ከምዕራፎቹ በአንዱ ማለትም ፍካትና ጥቃት በሚለው ሁለት የማይመሳሰሉ ርዕሰ ጉዳዮችን አቀራርቤአለሁ።
ምክንያት አለኝ። ፍካት ላይ ስለጉርምስና አንሥቼ ጤናማ ትምህርተ አውስቦትንም ነክቼ ሳበቃ ፆታዊ ጥቃት በሚለው ደመደምኩ። ከመዝጋቴ
በፊት ግን አሳሳቢ እየሆነ የመጣው የጉልበተኞች ጥቃት መጣልኝ። ማስከተሉም ተገቢና አስፈላጊ ሆኖ ታየኝ። እናም ቀጥዬበት ሁለቱን
አጎራበትኳቸው። አንባቢያን በዚህ ግር እንደማይሰኙም ተስፋ አለኝ።
ከዚህ መድብል ውስጥ እጅግ ጥቂቱ ከኔና ቤተሰቤ ተሞክሮ የተቆረሰ መሆኑን አስታውቃለሁ። ብዙው
አዎን ብዙው ግን ካነበብኩትና ካስተዋልኩት የተቀመመ ነው።
በቅርቡ ከሚታተመውና "ልጆች - የእግዚአብሔር ስጦታዎች " ከተሰኘው 13ኛ፡መጽሐፌ መግቢያ የተወሰደ
ዓለማየሁ ማሞ (አስፐን ሒል- ሜሪላንድ)
No comments:
Post a Comment