ልክ እንደታሰበው ሜትር አርቲስት አፈወርቅ በአፍሪካና የዕብራይስጥ ንባብ ክፍል ውስጥ ሰፋ ያለ ንግግር አደረጉ። አንደበተ ርቱዕ መሆናቸውን ደግሜ አስተዋልኩ። በዕለቱ ካነሷቸው ገጠመኞች ሁሉ የገረመኝ ከዚያም በፊት ያልሰማሁት ስለአንድ የሥዕል ሥራ ጨረታ ያወሱት ነው። በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን ለአንድ የሥዕል ሥራ ጨረታ ይወጣና የኢጣሊያ ተወላጅ የሆነ ሠዓሊ በ300000 ብር ሊሠራው ይስማማል። ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ደግሞ በተሻለ አኳኋን እና በተፈለገው የጊዜ ገደብ እሠራዋለሁና ለውጭ ዜጋ አይሰጥ ብለው ይማጸናሉ። ጩኸታቸው ሰሚ ያገኝናም ሥራው ይሰጣቸዋል። ሠርተው ያስረክባሉ። ግን ያገኙት ክፍያ የለም። ኋላ ነገሩ ከንክኖአቸው ለአንድ የንጉሡ ባለሟል ነገሩን ሲያማክሩ የተሰጣቸው መልስ የሚከተለው ነበር። “ ያልተከፈለህ በዝንጋኤ አይደለም፤ አገርህ በነጻ አስተምራሃለች። እንደውጪ ዜጋ ገንዘብ አትመኝ!”።
ከፕሮግራሙ በኋላ ቡናው እኔ ነኝ ያለ ምሳ አስከትሎ መጣ። እኔም ራሴን ከሜትር አርቲስት አፈወርቅ ኋላ አገኘሁት። ሰላም አልኳቸው። ጥቂትም አወራን።
በዓመቱ ወደአገር ቤት ለአስቸኳይ ጉዳይ ሄድኩ። ከ11 ዓመት በኋላ በመመለሴም ለስብሰባ የሚሆን ትርፍ ጊዜ አልነበረኝም። ግን ያን የሚያፋልስ አንድ ሁኔታ ተፈጠረ።
በአንድ ቀትር በጊዜያዊ ሞባይሌ “ሄሎ” አልኩ ቀበና ቆሜ። ያናገርኩት ጌታቸው በለጠን ነበር። በሚቀጥለው ቀን ስቴዲየም ዙሪያ እሄድ ስለነበር ቢሮው ጎራ ለማለት ነበር ዕቅዴ። ደራሲው ወዳጄ ግን በስልክ ያናገረኝ አባይ ዳር ቆሞ ነው።
“ሳላገኝህ መሄዴ ነዋ!” አልኩት ከሰላምታ በኋላ።
“ ስብሰባው ላይ ብትመጣና ብንተያይ ደስ ይለኛል። እንደምንም ብለህ...” አለና ለመጀመሪያ ጊዜ በአገራችን ስለሚካሄደው ዓለማቀፍ የደራሲያን ጉባዔ ማብራሪያ ሰጠኝ።
“ እሞክራለሁ” ብዬ ቃል ገባሁ። የዚህ ዓይነቱን ስብሰባ ለመካፈል ከጎረቤት ኬንያ ጀምሮ እስከናይጄሪያ ከለንደን እስከዋሽንግተን ያልተጋበዝኩበት ደግሞም ያልሄድኩበት አልነበረም። ዛሬ አዲሳበባ ላይ ተደግሶ ሲጠብቀኝ የማልቋደስበት ምክንያት አልታየኝም።
እናም በዚሁ መሠረት ግንቦት 2 2011 (እ.ኤ.አ) በኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ፕሬዚዳንት ግብዣ ይህንን ታሪካዊ ጉባኤ ለመካፈል እግረ መንገዴንም የናፈቁኝን ጸሓፍት ሰላም ለማለት ወደማዘጋጃ ቤቱ የባሕል አዳራሽ አመራሁ። ወደአዳራሹ ዘልቄ ዓይኔን ከጨለማው ካለማመድኩ በኋላ የማውቃቸውን ፍለጋ ዙሪያውን አማተርኩ። ማንም የለም። ከመላው አፍሪካ የመጡትን ጸሓፍትም ገረመምኩ። ከዚህ በፊት አብረውኝ እየዋሉና እያደሩ የደራሲያን ጉባኤ ከተካፈሉት እንኳ አንዳቸውን ማየት አልተቻለኝም። ለሻይ እረፍት ስንወጣ ጥቂት የማይባሉ ወዳጆቼን ባላገኝማ ባዶዬን ልሰናበት ነበር። ለክብር እንግዶች የተተውትን አንደኛና ሁለተኛ ረድፍ ወንበሮች አልፌ መሃል ተቀመጥኩ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ በአቅራቢያዬ የተቀመጡት ሰዎች ቀስ በቀስ እየታወሱኝ መጡ። ከ11 ዓመታት በኋላ ነው የማያቸው። ለብዙዎቹ በተቀመጥኩበት እጄን እያነሳሁ ሰላምታ ስሰጥ ቆይቼ ነበር። ጠና ካሉት የጥበብ ሰዎች ተርታ የተቀመጡትን ታላቅ ሰው ስመለከት ግን ያን ለማድረግ አልደፈርኩም። ተነስቼ ያሉበት ድረስ በመሄድ እጃቸውን ጨበጥኩ።
“ ሰላም ነህ ወዳጄ?” አሉኝ።
“ እንደዚህ ዓመት ሰላም ሆኜ አላውቅም፤ እርስዎስ?”
“ ምንም አልል፤ አጠፋሁህ መሰል ማን ልበል” አሉኝ።
“ ባለፈው ሐምሌ በኮንግረስ ቤተ መጻሕፍት አግኝቼዎት ነበር” አልኳቸው ስለራሴ ጥቂት ከተናገርኩ በኋላ።
“ አይ የኔ ነገር!” አሉ ታላቁ ሰው ከልባቸው እየሳቁ።
ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ የመሳቁ ተራ የኔ ሆነ። በአሜሪካ የኮንግረስ ቤተ መጻሕፍት ከፍተኛ ኃላፊነት ያለኝ ሰው መሆኔን በመጥቀስ አብረዋቸው ካሉ ጋር ያስተዋውቁኝ ጀመር። አሜሪካ ብኖርም እሳቸው የሚሉት ሰው እኔ አለመሆኔን ለማስረዳት ተራ ስጠብቅ ደግሞ ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተጠሩ። የፓን አፍሪካ ደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት ፊተኛውን ወንበር እንዲይዙ በክብር ጋበዟቸው። ከዚህም የተነሳ የመክፈቻውን ሥርዓት ከሥልጣኔ ሳልሻር ተካፈልኩ። አንዳንዶቹም ሄጄ እሳቸው አጠገብ እንድሰየም በጣታቸው ያመለክቱኝ ነበር። አሜሪካ ከተመለስኩ በኋላ ያ ክብር የሚገባውን ወዳጄን ( አቶ ፈንታሁን ጥሩነህ) ደውዬ ሳጫውተው ከልቡ ሳቀ። አሁን በሥራቸውም በቀልዳቸውም ያዋዙን እኒያ ታላቅ ሰው የሉም። እንኳንም ያኔ አገኘኋቸው!
No comments:
Post a Comment