ሰሞኑን ከተዘከሩት አሰቃቂ የታሪክ ዕውነቶች አንዱ ታይታኒክ የተሰኘችው መርከብ የሰጠመችበት መቶኛ ዓመት ነው። “ ተንሳፋፊዋ ከተማ” ከጨዋታ ውጭ የሆነችበትን ክፉ አጋጣሚ ስናስብ ቢያንስ ሁለት ነገሮችን ለመስማት ጓጉቼ ነበር። የመጀመሪያው 3547 የማሳፈር አቅም ኖሯት 1600 ሰዎችን ብቻ ይዛ በመስጠሟ 1947 ያህል ሰዎች ያህል ከጊዜአዊ ሞት መትረፋቸውን ነው። ለግንባታዋ 7.5 ሚሊዮን ዶላር ያፈሰሱት ባለሃብቶች የነበራቸው እስከ ግብአተ ባሕሯ ያልተቋረጠ ትምክህት ሌላው ትኩረቴ ነው። የጊዜውን ከፍተኛ ቴክኖሎጂ ታጥቃለችና ልትሰጥም አትችልም ሲሉ ከርመው ነበር። ያም በሚያዚያ 14፣ 1912 ፉርሽ ሆኗል። ይህን ትልቅ አሳዛኝ አጋጣሚ በሲኒማ ለማየት ወደሲልቨር ስፕሪንግ ከመውረዴ በፊት ግን ቀጣዩን የሲድኒ ዶብል ግጥም ለአንባቢዎቼ ማቅረብ ወደድኩ። ከትርጉምነቱም ባሻገር ለምርጫዬ ሁለት ምክንያቶች አሉኝ። አንደኛ ጠያቂዋ እናት በታይታኒክ ላይ የሚሰራ ልጇን ደኅንነት የምታጣራ የሚያስመስል ድምጸት አላት። ሁለተኛው ደግሞ በአፍላ ዕድሜአቸው የረገፉትን መርከበኞች ጓዶቼን ስለሚያስታውሰኝ ነው!
ልጄ እንዴት ነው???
መርከበኛው ፤መርከበኛው፤
ልጄ- ልጄ እንዴት ነው?
“አንቺ እመቤት የልጅሽን ስም ንገሪኝ፤
የትኛውስ መርከብ ላይ ነው እሱ እሚገኝ?”
“ልጄ ጆኒ ወደባሕር የተጓዘው፤
ስለመርከቡ ምን ይገደኝ ባሕረኛው?
ልጄ እንደሆን የኔ ልጅ ነው፤
“በርግጥ ከባሕር ነው የመጣኽው?
የኔን ጆኒ የማታውቀው፤
ጠይቄ ቢሆን የመንገድ ሰው፤
በመንደሩ ከሚዞረው፤
አንድም የለ ከጉባኤው፤
ልጄን ጆኒን የማያውቀው፤
“ልጄ- ልጄ እንዴት ነው?
ካልነገርከኝ በስተቀረ በደንበኛ፤
እምላለሁ እንዳልሆንክ መርከበኛ።
ሰማያዊ ጃኬት ወይም መልሕቅ፤
መርከበኛው በል ተጠየቅ።
አብረቅራቂ ቁልፍ ወይም ዘውድ፤
ከአንዳቸው ተዛመድ።
አዎ መርከቡ እንኳ ስሟ ነበር “ቀዮ”፤
“ቀስ ብለሽ አውሪ ቀስ በይ ሴትዮ”።
“ለምን ቀስ እላለሁ መርከበኛው፤
ስለልጄ ጆኒኮ ነው እማወራው?
እንደኩራቴ ድምፄ ይጉላ፤
በመንደሩ ላዚምለት በሞላ።
ለምን ብዬ ቀስ እላለሁ በእውነቱ፤
“ምክንያቱም ሰጥማለቻ መርከቢቱ”።
ስለመስጠሟ ምን አገባኝ መርከበኛው፤
“ልጄ- ልጄ ጆኒ እንዴት ነው?
መሬት ትንካ ቢሻት ትዋኝ፤
ትስመጥ ወይ ትንሳፈፍ እኔን አያገባኝ።
ተሳፍሬያት አላውቅ ለአንድ ቀን እንኳን፤
ይልቅ ይጭነቃቸው ባለቤቶችዋን።
እኔ ግን የምለው፤
ልጄ ጆኒ እንዴት ነው?
“መርከቧ ላይ የነበሩ ሁሉም ተሳፋሪ፤
አብረዋት ሰጠሙ የለም አንድ ቀሪ”።
“ልጄ- ልጄ እንዴት ነው?
እኔ ስለነርሱ ምን ቸገረኝ፤
እናታቸው አይደለሁኝ፤
ሌላ ሳይሆን ስለእርሱ ብቻ ንገረኝ።
ልጄ- ልጄ እንዴት ነው?