Wednesday, April 18, 2012

መርከበኛው ፤መርከበኛው፤


ሰሞኑን ከተዘከሩት አሰቃቂ የታሪክ ዕውነቶች አንዱ ታይታኒክ የተሰኘችው መርከብ የሰጠመችበት መቶኛ ዓመት ነው። “ ተንሳፋፊዋ ከተማ” ከጨዋታ ውጭ የሆነችበትን ክፉ አጋጣሚ ስናስብ ቢያንስ ሁለት ነገሮችን ለመስማት ጓጉቼ ነበር። የመጀመሪያው  3547 የማሳፈር አቅም ኖሯት  1600 ሰዎችን ብቻ ይዛ በመስጠሟ 1947 ያህል ሰዎች ያህል ከጊዜአዊ ሞት መትረፋቸውን ነው። ለግንባታዋ 7.5 ሚሊዮን ዶላር ያፈሰሱት ባለሃብቶች የነበራቸው እስከ ግብአተ ባሕሯ ያልተቋረጠ ትምክህት ሌላው ትኩረቴ ነው። የጊዜውን ከፍተኛ ቴክኖሎጂ ታጥቃለችና ልትሰጥም አትችልም ሲሉ ከርመው ነበር። ያም በሚያዚያ 14፣ 1912 ፉርሽ ሆኗል። ይህን ትልቅ አሳዛኝ አጋጣሚ በሲኒማ ለማየት ወደሲልቨር ስፕሪንግ ከመውረዴ በፊት ግን ቀጣዩን የሲድኒ ዶብል ግጥም ለአንባቢዎቼ ማቅረብ ወደድኩ። ከትርጉምነቱም ባሻገር ለምርጫዬ ሁለት ምክንያቶች አሉኝ። አንደኛ ጠያቂዋ እናት በታይታኒክ ላይ የሚሰራ ልጇን ደኅንነት የምታጣራ የሚያስመስል ድምጸት አላት። ሁለተኛው ደግሞ በአፍላ ዕድሜአቸው የረገፉትን መርከበኞች ጓዶቼን  ስለሚያስታውሰኝ ነው!

 ልጄ እንዴት ነው???
መርከበኛው ፤መርከበኛው፤
ልጄ- ልጄ እንዴት ነው?
“አንቺ እመቤት የልጅሽን ስም ንገሪኝ፤ 
የትኛውስ መርከብ ላይ ነው እሱ እሚገኝ?”
“ልጄ ጆኒ ወደባሕር የተጓዘው፤
ስለመርከቡ ምን ይገደኝ ባሕረኛው?
ልጄ እንደሆን የኔ ልጅ ነው፤
“በርግጥ ከባሕር ነው የመጣኽው?
የኔን ጆኒ የማታውቀው፤
ጠይቄ ቢሆን የመንገድ ሰው፤
በመንደሩ ከሚዞረው፤
አንድም የለ ከጉባኤው፤
ልጄን ጆኒን የማያውቀው፤
“ልጄ- ልጄ እንዴት ነው?
ካልነገርከኝ በስተቀረ በደንበኛ፤
እምላለሁ እንዳልሆንክ መርከበኛ።
ሰማያዊ ጃኬት ወይም መልሕቅ፤
መርከበኛው በል ተጠየቅ።
አብረቅራቂ ቁልፍ ወይም ዘውድ፤
ከአንዳቸው ተዛመድ። 
አዎ መርከቡ እንኳ ስሟ ነበር “ቀዮ”፤
“ቀስ ብለሽ አውሪ ቀስ በይ ሴትዮ”።
“ለምን ቀስ እላለሁ መርከበኛው፤
ስለልጄ ጆኒኮ ነው እማወራው?
እንደኩራቴ ድምፄ ይጉላ፤
በመንደሩ ላዚምለት በሞላ።
ለምን ብዬ ቀስ እላለሁ በእውነቱ፤
“ምክንያቱም ሰጥማለቻ መርከቢቱ”።
ስለመስጠሟ ምን አገባኝ መርከበኛው፤
“ልጄ- ልጄ ጆኒ እንዴት ነው? 
መሬት ትንካ ቢሻት ትዋኝ፤
ትስመጥ ወይ ትንሳፈፍ እኔን አያገባኝ።
ተሳፍሬያት አላውቅ ለአንድ ቀን እንኳን፤ 
ይልቅ ይጭነቃቸው ባለቤቶችዋን።
እኔ ግን የምለው፤
ልጄ ጆኒ እንዴት ነው?
“መርከቧ ላይ የነበሩ ሁሉም ተሳፋሪ፤  
አብረዋት ሰጠሙ የለም አንድ ቀሪ”።
“ልጄ- ልጄ እንዴት ነው?
እኔ ስለነርሱ ምን ቸገረኝ፤
እናታቸው አይደለሁኝ፤
ሌላ ሳይሆን ስለእርሱ ብቻ ንገረኝ።
ልጄ- ልጄ እንዴት ነው?

Friday, April 13, 2012

ታላቁ ሠዓሊ የተውልኝ ትዝታ

በሐምሌ ወር 2010 (እ.ኤ.አ) አንድ ጥሪ በኢሜይል ደረሰኝ። በአሜሪካ የኮንግረስ ቤተ መጻሕፍት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌን በክብር እንግድነት እንደጋበዘ ይገልጻል። ዋናው ዓላማም አንጋፋው ሠዓሊ የሕይወት ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ መሆኑን ይጠቅሳል። የምሳ ዕረፍቴን ተጠቅሜ ፕሮግራሙን ለመካፈል ወሰንኩ። ብዙም ሳይቆይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መርሓ ግብሩን ስፖንሰር ማድረጉን ሰማሁ። የቡና ቅምሻ እንደሚኖርም አረጋገጥኩ። እነዚህ ሁሉ እንድሄድ አበረቱኝ።
ልክ እንደታሰበው ሜትር አርቲስት አፈወርቅ በአፍሪካና የዕብራይስጥ ንባብ ክፍል ውስጥ ሰፋ ያለ ንግግር አደረጉ። አንደበተ ርቱዕ መሆናቸውን ደግሜ አስተዋልኩ። በዕለቱ ካነሷቸው ገጠመኞች ሁሉ የገረመኝ ከዚያም በፊት ያልሰማሁት ስለአንድ የሥዕል ሥራ ጨረታ ያወሱት ነው። በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን ለአንድ የሥዕል ሥራ ጨረታ ይወጣና የኢጣሊያ ተወላጅ የሆነ ሠዓሊ በ300000 ብር ሊሠራው ይስማማል። ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ደግሞ በተሻለ አኳኋን እና በተፈለገው የጊዜ ገደብ እሠራዋለሁና ለውጭ ዜጋ አይሰጥ ብለው ይማጸናሉ። ጩኸታቸው ሰሚ ያገኝናም ሥራው ይሰጣቸዋል። ሠርተው ያስረክባሉ። ግን ያገኙት ክፍያ የለም። ኋላ ነገሩ ከንክኖአቸው ለአንድ የንጉሡ ባለሟል ነገሩን ሲያማክሩ የተሰጣቸው መልስ የሚከተለው ነበር። “ ያልተከፈለህ በዝንጋኤ አይደለም፤ አገርህ በነጻ አስተምራሃለች። እንደውጪ ዜጋ ገንዘብ አትመኝ!”።
ከፕሮግራሙ በኋላ ቡናው እኔ ነኝ ያለ ምሳ አስከትሎ መጣ። እኔም ራሴን ከሜትር አርቲስት አፈወርቅ ኋላ አገኘሁት። ሰላም አልኳቸው። ጥቂትም አወራን።
በዓመቱ ወደአገር ቤት ለአስቸኳይ ጉዳይ ሄድኩ። ከ11 ዓመት በኋላ በመመለሴም ለስብሰባ የሚሆን ትርፍ ጊዜ አልነበረኝም። ግን ያን የሚያፋልስ አንድ ሁኔታ ተፈጠረ።
በአንድ ቀትር በጊዜያዊ ሞባይሌ “ሄሎ” አልኩ ቀበና ቆሜ። ያናገርኩት ጌታቸው በለጠን ነበር። በሚቀጥለው ቀን ስቴዲየም ዙሪያ እሄድ ስለነበር ቢሮው ጎራ ለማለት ነበር ዕቅዴ። ደራሲው ወዳጄ ግን በስልክ ያናገረኝ አባይ ዳር ቆሞ ነው።
“ሳላገኝህ መሄዴ ነዋ!” አልኩት ከሰላምታ በኋላ።
“ ስብሰባው ላይ ብትመጣና ብንተያይ ደስ ይለኛል። እንደምንም ብለህ...” አለና ለመጀመሪያ ጊዜ በአገራችን ስለሚካሄደው ዓለማቀፍ የደራሲያን ጉባዔ ማብራሪያ ሰጠኝ።
“ እሞክራለሁ” ብዬ ቃል ገባሁ። የዚህ ዓይነቱን ስብሰባ ለመካፈል ከጎረቤት ኬንያ ጀምሮ እስከናይጄሪያ ከለንደን እስከዋሽንግተን ያልተጋበዝኩበት ደግሞም ያልሄድኩበት አልነበረም። ዛሬ አዲሳበባ ላይ ተደግሶ ሲጠብቀኝ የማልቋደስበት ምክንያት አልታየኝም።

እናም በዚሁ መሠረት ግንቦት 2 2011 (እ.ኤ.አ) በኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ፕሬዚዳንት ግብዣ ይህንን ታሪካዊ ጉባኤ ለመካፈል እግረ መንገዴንም የናፈቁኝን ጸሓፍት ሰላም ለማለት ወደማዘጋጃ ቤቱ የባሕል አዳራሽ አመራሁ። ወደአዳራሹ ዘልቄ ዓይኔን ከጨለማው ካለማመድኩ በኋላ የማውቃቸውን ፍለጋ ዙሪያውን አማተርኩ። ማንም የለም። ከመላው አፍሪካ የመጡትን ጸሓፍትም ገረመምኩ። ከዚህ በፊት አብረውኝ እየዋሉና እያደሩ የደራሲያን ጉባኤ ከተካፈሉት እንኳ አንዳቸውን ማየት አልተቻለኝም። ለሻይ እረፍት ስንወጣ ጥቂት የማይባሉ ወዳጆቼን ባላገኝማ ባዶዬን ልሰናበት ነበር። ለክብር እንግዶች የተተውትን አንደኛና ሁለተኛ ረድፍ ወንበሮች አልፌ መሃል ተቀመጥኩ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ በአቅራቢያዬ የተቀመጡት ሰዎች ቀስ በቀስ እየታወሱኝ መጡ። ከ11 ዓመታት በኋላ ነው የማያቸው። ለብዙዎቹ በተቀመጥኩበት እጄን እያነሳሁ ሰላምታ ስሰጥ ቆይቼ ነበር። ጠና ካሉት የጥበብ ሰዎች ተርታ የተቀመጡትን ታላቅ ሰው ስመለከት ግን ያን ለማድረግ አልደፈርኩም። ተነስቼ ያሉበት ድረስ በመሄድ እጃቸውን ጨበጥኩ።
“ ሰላም ነህ ወዳጄ?” አሉኝ።
“ እንደዚህ ዓመት ሰላም ሆኜ አላውቅም፤ እርስዎስ?”
“ ምንም አልል፤ አጠፋሁህ መሰል ማን ልበል” አሉኝ።
“ ባለፈው ሐምሌ በኮንግረስ ቤተ መጻሕፍት አግኝቼዎት ነበር” አልኳቸው ስለራሴ ጥቂት ከተናገርኩ በኋላ።
“ አይ የኔ ነገር!” አሉ ታላቁ ሰው ከልባቸው እየሳቁ።
ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ የመሳቁ ተራ የኔ ሆነ። በአሜሪካ የኮንግረስ ቤተ መጻሕፍት ከፍተኛ ኃላፊነት ያለኝ ሰው መሆኔን በመጥቀስ አብረዋቸው ካሉ ጋር ያስተዋውቁኝ ጀመር። አሜሪካ ብኖርም እሳቸው የሚሉት ሰው እኔ አለመሆኔን ለማስረዳት ተራ ስጠብቅ ደግሞ ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተጠሩ። የፓን አፍሪካ ደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት ፊተኛውን ወንበር እንዲይዙ በክብር ጋበዟቸው። ከዚህም የተነሳ የመክፈቻውን ሥርዓት ከሥልጣኔ ሳልሻር ተካፈልኩ። አንዳንዶቹም ሄጄ እሳቸው አጠገብ እንድሰየም በጣታቸው ያመለክቱኝ ነበር። አሜሪካ ከተመለስኩ በኋላ ያ ክብር የሚገባውን ወዳጄን ( አቶ ፈንታሁን ጥሩነህ) ደውዬ ሳጫውተው ከልቡ ሳቀ። አሁን በሥራቸውም በቀልዳቸውም ያዋዙን እኒያ ታላቅ ሰው የሉም። እንኳንም ያኔ አገኘኋቸው!    

Saturday, March 31, 2012

እዚሁ እንገናኝ!

ጊዜ ባገኝ፤
የማደርገውን አውቃለሁኝ፤
የመጻሕፍቴ ገጾች ወደቅን እስኪሉኝ፤
አነባቸው ነበር እየደጋገምኩኝ።
ጊዜ ባገኝ
እጽፍ ነበር በርካታ ደብዳቤዎች፤ 
ያልመለስኳቸውን ለብዙ ሳምንቶች፤
ለብዙ ብዙ ሰዎች።
ጊዜ ባገኝ
እከፍል ነበር የስልኬን ወረት፤
ያጠራቀምኩትን ለሳምንታት፤
ደግሜም አልዘገይ በውነት።
ጊዜ ባገኝ
ሕይወቴን እቃኛለሁ በዚያ፤
ጊዜ ይኖረኝ ዘንድ መግባቢያ፤
ከሚስቴ ጋር መቀራረቢያ።
ጊዜ ባገኝ
ግሩም የደስታ ሕልም፤
ከወር ከዓመት ከአስር ዓመት በኋላ ወይም፤
ግን ይህን መጨረስ አልችልም፤
 ምክንያቱም ጊዜ የለኝም። 

ገጣሚው ቶማስ ኤል ሜሰን እንዳለው እኔም ጊዜ ሳገኝ እያልኩ ያዘገየሁት አንድ አሳብ ነበረኝ። ይኸውም አንድ የጽሑፍ ሠሌዳ( Blog) ከፍቼ አንዳንድ አሳቦችን ከናንተ ጋር መካፈል ነው። ዛሬ ሞላልኝ። ዳር ላይ ቆሜ ሳመነታ “ትችላለህ” ብላ ወደዚሁ የገፋችኝን ብሌንን ላመሰግን ይገባኛል። ይህንኑ የጽሑፍ ሠሌዳ “ከአለፍ አገደም” ብዬ ሰይሜዋለሁ። ምክንያቱ አሁንም  የጊዜ ጉዳይ ብቻ መሆኑ ይሰመርበት። ከተማሪነቴ ከሙሉ ጊዜ ሥራዬ አልፎ አልፎ ከምሠራው የማስተርጎም ሥራ ቤተሰብ ከማስተዳደሩና መጻሕፍትን ከማዘጋጀቱ ባሻገር መሆኑ ነው። ስለሆነም ከአለፍ አገደም እዚሁ እንገናኝ! በአጋጣሚ በዚህ ያላካተትኳቸውና ቢያነቡ አይጠሉም የምትሏቸው ቢኖሩ መልዕክቱን አድርሱላቸው ስል በትሕትና እጠይቃችኋለሁ።
ወዳጃችሁ
ዓለማየሁ ማሞ


http://alemayehuwrites.blogspot.com/

Tuesday, March 27, 2012

ስብሐት ገብረእግዚአብሔርን በትውስታ


ከጋሼ ስብሐት ጋር በትልቅ ርቀት እንተዋወቅ ነበር። ትውውቁን የፈጠረው ቢያንስ ለሦስት ዓመታት በዕለታዊ ጋዜጣ ላይ አብረን መሥራታችን ነው። ርቀቱን ያስከተለው ደግሞ ልዩነታችን ነበር። እርሱ ትልቅ እኔ ትንሽ፤እርሱ አገር የሚያውቀው ጥበብ አሳማሪ እኔ ደግሞ የመስሪያ ቤታችን ፈታሾች እንኳ ደባብሰው የሚያስገቡኝ ጀማሪ እርሱ በጎልማሳነት ዕድሜ ያለ ሰው እኔ ቢያንስ በሦስት አስር ዓመታት የማንሰው እርሱ በመስኩ የተማረ እኔ ወደኮሌጅ ፊቴ ያልዞረ.. ወ.ዘ.ተ ስለነበርን ብቻ ነው። በነዚያ ሦስት ዓመታት ግን ስለእርሱ ሦስት የሚያክሉ ገጠመኞች አሉኝ። ለዛሬ የማነሳው መቼውንም የማልረሣው ገጠመኝ ግን ይሄ ነው። አንድ ማለዳ ወደቢሮዬ ...ይመጣል። ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ

“ ዓለማየሁ ነው እሚሉህ አይደል?” ይለኛል።

“ ዓለማየሁ ማሞ” አልኩት ሁለት ስለነበርን

“ አንድ ጥያቄ አለኝ?”

“ ምን?” አልኩ በብዙ ጥርጣሬ

“ መጽሐፍ ቅዱስ ታነባለህ አሉ”

“ልክ ነው፡ ጥያቄህ ስለርሱ ነው?”

“ኢየሱስ ነጋዴዎችን በጅራፍ ያባረረው የትኛው ቦታ ላይ ነው?”

“እዚህ ጋ” አልኩት በስተኋላ ከእበላ ባዮች ብዙ ስደት ያመጣችብኝን መጽሐፍ ከመሳቢያዬ ውስጥ አውጥቼ።

ከአንገቱ ዝቅ ብሎ አመስግኖኝ ወጣ። ከመካከላችን ትልቁ ሰውዬ ያሳየኝ ትኅትና መቼውንም የምዘነጋው አይደለም። በበነጋው እግረ መንገድ ላይ ያችን ጥቅስ ተጠቅሞና ኢየሱስን ከቼጉቬራ ጋር አነጻጽሮ አስቂኝ ጽሑፍ አሰፈረ። እያመመኝ አነበብኩት። ምክንያቱም ኢየሱስ በዚያን ዘመን ለእኔ ከታላላቅ የሃይማኖት መሪዎች አንዱ ብቻ ሳይሆን ብቸኛ አዳኝም ነበር። አሁንም ነው! ግን ሳገኘው ያስለመድኩትን የአክብሮት ሰላምታ አላጓደልኩም። ለምን ቢሉ አንድም ያመነበትን የመጻፍ መብቱን አክብሬ አልያም ባየሁበት ትኅትና ተሰብሬ።

ርቀታችን ብዙ ሰፍቶ ብዙም ሳይቆይ ፕሬስን ስለቅ የግንኙነታችን ርቀት ጨመረ። በ2001( እ.አ.አ) ወደአሜሪካ ስመጣ ደግሞ ላንተያይ ተለያየን። ከ10 ወራት በፊት በአዲስ አበባ ቆይታዬ የአፍሪካ ደራሲያንን ዓለም አቀፍ ጉባኤ ተካፍዬ ነበር። በዚያ የጋሼ ስብሃትን ማስታወሻ ያሳተመውን ዘነበ ወላን ጨምሮ በርካታ የሥነ ጽሑፍ ሰዎችን እንጂ አርሱን አላየሁትም። ባየው እወድ ነበር። አልሆነም። ርቀቱ በዚህ ምድር ብቻ ሳይሆን በሁለት ዓለማት መካከል ሆኖአልና
!